ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሻሸመኔ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ፕሪሚየር ሊጉን የሚሰናበቱበትን የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ ያደርጋሉ፡፡ ሀምበሪቾ ዱራሜ እስካሁን ካደረጋቸው 29 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡
ቡድኑ እስካሁን በ22 ጨዋታዎች ተሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ 54 ግብ ተቆጥሮበት በ43 የግብ ዕዳ ዘጠኝ ነጥብ ብቻ በመያዝ መውረዱን ቀደም ሲል አረጋግጧል፡፡ ቡድኑ 16ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በመጣበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ መመለሱ ቀደም ሲል ተረጋግጧል፡፡
ዛሬ ተጋጣሚው ሻሸመኔ ከተማ ካደረጋቸው 29 ጨዋታዎች 41 ግብ ተቆጥሮበት 22 የግብ ዕዳ በመያዝ በ14 ነጥብ 15ኛ ደረጃን በመያዝ መውረዱ የታወቀው ቀደም ሲል ነው፡፡ ሻሸመኔ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ዛሬ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ምሽት 12 የሚያደርጉት ጨዋታ የመርሐግብር ማሟያ ሲኾን ማንም አሸነፈ ቡድኖቹ ፕሪሚየር ሊጉን ይሰናበታሉ፡፡
ቀን 9 ሰዓት በፕሪሚየር ሊጉ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ እና 14ኛ ላይ የተቀመጠው ወልቂጤ ከተማ ይጫዎታሉ፡፡ አዳማ ከተማ ጨዋታውን ካሸነፈ ደረጃውን በአንድ የሚያሻሽል ይኾናል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!