ፊል ፎደን በአሠልጣኙ ጋሬት ሳውዝጌት ላይ የተፈጠረው ጫና ትክክል አይደለም አለ።

0
378

ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሳውዝጌት ቡድን በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያውን በአንደኝነት አጠናቋል። በጥሎ ማለፉ ደግሞ በጭማሪ ደቂቃ ስሎቫኪያን በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል ችሏል። ይሁን እንጂ ብሔራዊ ቡድኑ የተጫወተበት መንገድ፣ በተለይም የቡድን አወቃቀሩ እና የሚከተለው የጨዋታ ታክቲክ በርካታ ትችቶችን እያስተናገደ ይገኛል። እነዚህ ትችቶች አሠልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌትን ጫና ውስጥ እንደከተታቸውም እየተገለጸ ነው።

የእንግሊዙ የፊት መስመር ተጫዋች ፊል ፎደን በአሠልጣኙ ጋሬት ሳውዝጌት ላይ የተፈጠረው ጫና እንደሚያሳዝነው ተናግሯል። “የተወሰነውን ወቀሳ እኛ ተጫዋቾችም መውሰድ ይኖርብናል” ብሏል ፎደን። ስለ ሳውዝጌት እና ቅዳሜ ከስዊዘርላንድ ጋር ስለሚኖረው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ የተጠየቀው የማንቸስተር ሲቲው ተጫዋች “ስለ ሳውዝጌት አዝናለሁ፤ በልምምድ ጊዜ ተጭነን እንድንጫወት ነው የሚነግረን ሲል ሀሳብ ሰጥቷል።

ፎደን አሠልጣኙ የሚችለውን እንዳደረገ እና የተሻለ መፍትሄ ማምጣት ላይ ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መኾኑንም ተናግሯል። ፎደን የፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ያሸነፈ ቢኾንም በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ግን እስካሁን ለብሔራዊ ቡድኑ ግብ አላስቆጠረም። በእንቅስቃሴ ደረጃም ከሚተቹ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።

ከምድብ ማጠሪያ ጨዋታዎች ጀምሮ አቋሜ እየተሻሻለ ነው የመጣው ያለው የ24 ዓመቱ ፎደን በቀሪ ጨዋታዎች የተሻለ ብቃት እንደሚያሳይ ተስፍውን ገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here