ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ዋንጫ በድምቀት ቀጥሏል። ሚዲያዎችም ስለብሔራዊ ቡድኖች እና ተጫዋቾች ዘገባዎችን በሰፊው እየሠሩ ነው። ጎን ለጎን የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ እየተካሄደ ነው። ውድድሩ ብራዚል እና አርጀንቲናን የመሳሰሉ ትልልቅ ቡድኖች ያሉበት ነው።
በተጫዋችም ሊዮኔል መሲ፣ ቪኒሲየስ ጁኔር እና ለውታሮ ማርቲኔዝን በመሳሰሉ ኮከቦች የተሞላ ነው። ነገር ከኮፓ አሜሪካ ይልቅ ስለአውሮፓ ዋንጫ፣ ስለ መሲ ሳይኾን ስለሮናልዶ በስፍት እየተወራ ነው። ቢቢሲ ውድድሩ ከአውሮፓ ዋንጫ ጋር በተመሳሳይ ወቅት መካሄዱ እንዲደበዝዝ አድርጎታል ባይ ነው።
የዘንድሮው የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ በዩናይትድ ስቴትስ አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል። 16 ሀገራትን እያሳተፈ ሲኾን፣ ከሰሜን አሜሪካ አዘጋጇ አሜሪካን ጨምሮ ካናዳ እና ሜክሲኮን በተጋባዥነት አሳትፏል።
የኮፓ አሜሪካው አሁን ከየምድብ ያለፉ ስምንት ሀገራትን ለይቷል። ምድብ አንድ ሊዮኔል መሲን የያዘችው አርጀንቲና የምድቧ አሸናፊ ኾናለች። አርጀንቲና የምድብ ሦስቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ዘጠኝ ነጥብ ይዛለች። የኢንተር ሚላኑ አጥቂ ላውታሮ ማርቲኔዝ በምድብ ጨዋታዎች ለሀገሩ ምርጥ ብቃት አሳይቷል። ካናዳ አርጀንቲናን በመከተል ከምድብ አንድ ለጥሎ ማለፍ የበቃች ሀገር ናት።
ምድብ ሁለትን ያልተጠበቀችው ቬንዚውላ የበላይ ኾና አጠናቃ አለች። ኢኳዶር ተከታዮን ደረጃ በመያዝ ወደ ቀጣዩ ዙርም አልፋለች። አዘጋጇ አሜሪካ ከምድብ በተሰናበተችበት ምድብ ሦስት ኡራጋይ የምድቡ አሸናፊ ናት። ኡራጋይ የምድብ ጨዋታዎቿን በሙሉ ማሸነፍም ችላለች። ፓናማ በስድስት ነጥብ የዚህ ምድብ ሁለተኛ ናት።
ምድብ አራት የብራዚል መገኛ ነው። ከምድቧ አንድ ጨዋታ ብቻ ያሸነፈችው ብራዚል በሁለቱ ነጥብ ተጋርታለች። ምድቡን ኮሎምቢያ ናት በሰባት ነጥብ ያሸነፈችው።
አርጀንቲና ከሦስት ዓመት በፊት የተካሄደውን ውድድር ማሸነፏ ይታወሳል። ወድድሩን ብዙ ጊዜ በማሸነፍም ከኡራጋይ ጋር እኩል ባለታሪክ ናት። ሁለቱ ሀገራት ኮፓ አሜሪካን እኩል 15 ጊዜ አሸንፈዋል። ብራዚል ውድድሩን ዘጠኝ ጊዜ ማሸነፏን ቶፕንድ ስፖርት የተሰኘ የመረጃ ምንጭ አስነብቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!