ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአካል እንቅስቃሴ ተግባራትን ባሕል በማድረግ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን የመከላከሉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገልጸዋል። 20ኛው ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በእግር ጉዞ ፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና በደም ልገሳ መርሐግብር ተከብሯል።
መርሐግብሩን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ደም በመለገስ የማይተካውን የሰው ሕይወት የምናተርፍበት ስለኾነ ደም ለጋሾች ሊመሠገኑ ይገባል ብለዋል። ደም መለገስ ባሕል መኾን አለበት ያሉት ሚኒስትሯ ቀኑ የሚከበረው በደም እጦት ምክንያት ዜጎች ህይወታቸውን እንዳያጡ ደም መለገስ ባሕል እንዲኾን ለማስተማር እንደኾነም ገልጸዋል።
ዛሬ በእርምጃ ቀኑን እያሰቡ፣ ደም እየለገሱ የሰው ሕይወትን ማትረፍ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትሯ ይህ የእግር ጉዞ በየወሩ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ዶክተር መቅደስ በአካል እንቅስቃሴ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን መከላከል ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ደም እና ህብረህዋስ ባንክ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እጅግ ወሳኝ የህክምና ግብዓት የኾነውን ደም ለማሟላት ሰዎች በቋሚነት ደም መለገስ ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ፕሮግራሙ ቋሚ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የሚመሠገኑበት እና አዳዲስ ደም ለጋሾችን ለማፍራት ግንዛቤ የሚሰፋበት ነው ያሉት ዶክተር አሸናፊ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነፍሶችን ለመታደግ ደም የለገሳችሁ ሁሉ እናመሠግናለን ብለዋል። ለ60ኛ ጊዜ ደም የለገሱት ዳዊት ፍቅሩ መርሐግብሩ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በእጅጉ እንደሚጠቅም ገልጸው ኅብረተሰቡ ደም በመለገስ ሕይወትን እንዲታደግ ጥሪ ማቅረባቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!