“የብዙ አትሌቶች ተስፋ” ተንታ አትሌቲክስ መንደር።

0
341

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል በደቡብ ወሎ ዞን በተንታ ወረዳ ከባህር ጠለል በላይ ከ2400 እስከ 3000 ሜትር ከፍታ ቦታ ላይ ይገኛል። በተፈጥሯዊ ምቹነቱ ምክንያት በወረዳው በ2003 ዓ.ም የአትሌቶች ማሠልጠኛ ፕሮጀክት ተቋቁሟል። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በማሠልጠኛ ማዕከልነት አድጎ አትሌቶችን እያሠለጠነ ይገኛል። አሁን ላይ 57 አትሌቶች እየሠለጠኑበት ሲኾን አካባቢው ውጤታማ አትሌቶችን እያፈራ ነው።

በ3 ሺ ሜትር መሰናክል ኢትዮጵያን ወክላ የተወዳደረችው ሶፊያ አሠፋ እና እንግሊዝ ላይ በተደረገ የ10 ሺ ሜትር ውድድር የተሳተፈው ጀማል ይመርን ጨምሮ በርካታ ስኬታማ አትሌቶች አድገውበታል። ማዕከሉ በሀገር ውስጥ ውድድሮች ውጤታማ መኾኑን እና በማዕከሉ የሠለጠኑ ስምንት አትሌቶችም በውጪ ሀገር ውድድር የመካፈል እድል ያገኙ መኾናቸውን የተንታ ወረዳ ወጣቶች እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀይደር ሀሰን ገልጸዋል።

የወረዳው ወጣቶች እና ስፖርት ጽሕፈት ቤትም አካባቢው ለአትሌቲክስ ያለውን ምቾት በማሰብ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት 28 ልጆችን አሠልጣኝ መድቦ በፕሮጀክት እያሠለጠነ መኾኑን ነው ኀላፊው የገለጹት። አትሌት ስለናት ቢተው የማዕከሉ የ5 ሺህ ሜትር ርቀት ሠልጣኝ ናት። ወደ ማዕከሉ በ2014 ዓ.ም የተቀላቀለች ሲኾን በ10 ሺህ ሜትርም እየሞከርኩ ነው ብላለች። በቀጣይም በ10 ሺ ሜትር እና በ21 ኪሎ ሜትር የመሮጥ ዕቅድ አላት።

ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ የ6 ኪሎ ሜትር ውድድር በማድረግ የውድድር መድረኩን መልመድ መጀመሯን ገልጻለች። ይህን ቃለ መጠይቅ በምትሰጥበት ጊዜ ደግሞ ሀዋሳ ለሚደረገው ሀገር አቀፍ የወጣቶች ውድድር የማሠልጠኛ ክለቧን ወክላ ለመወዳደር በልምምድ ላይ ናት። ስለናት ተወልዳ ያደገችበት አዊ ዞን ለሩጫው ምቹ መልክዓ ምድር ስላለው ሩጫን ስትለማመድ መቆየቷን ገልጻ የቀጣይ ህልሟም በቅርቡ 21 ኪሎ ሜትር እና በረጅም ጊዜ ደግሞ ማራቶን በመሮጥ ውጤታማ መኾኑን ገልጻለች።

አትሌቷ በማሠልጠኛ ማዕከል ገብታ ስትሠለጥን ተንታ የመጀመሪያዋ መኾኑን ገልጻ አስፈላጊው ሁሉ እየተሟላልን ነው፤ የመሮጫ ትራክ ጥያቄያችንም ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው ብላለች። አትሌት በቃሉ አደመ ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ወረዳ ነው ተወልዶ ያደገው። በ2014 ዓ.ም ተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከልን ተቀላቅሎ እያሠለጠነ ይገኛል። በርዝመት ዝላይ እና በመቶ ሜትር ሩጫ በመሠልጠን ላይ ነው።

ከ1 ሺህ 500 እና ከ5 ሺህ ሜትር በመነሳት የማራቶን አሸናፊ የመኾን ህልም ያለው አትሌት በቃሉ በሁለት ዓመታት ቆይታው በውድድሮች ላይ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ጀምሯል። በአማራ ክልል የክለቦች ሻምፒዮና በርዝመት ዝላይ ሁለት ወርቅ እና በመቶ ሜትር ሩጫ የብር ሜዳልያ አሸንፏል፣ አሰላ ላይ በተደረገ ሀገር አቀፍ የመላ ኢትዮጵያ የማሠልጠኛ ማዕከላት ውድድር የአንድ ወርቅ እና የአንድ ብር ሜዳልያ ባለቤት ኾኗል፣ በሰኔ ወር ሀዋሳ ላይ በሚደረገው የመላ ኢትዮጵያ ወጣቶች ውድድር በርዝመት ዝላይ እና በመቶ ሜትር ሩጫ እየተወዳደረ ነው።

በማሠልጠኛ ማዕከሉ ደስተኛ መኾኑን የተናገረው አትሌት በቃሉ ሥልጠናውን በጥሩ ሁኔታ እያገኘ መኾኑን ተናግሯል። የአየር ንብረቱም የማሠልጠኛ ማዕከሉም ለአትሌቶች ምቹ መኾኑን ገልጿል። በማዕከሉ አትሌቶች አቋማቸውን እና ውጤታማነታቸውን ሲያሳድጉ ደመወዛቸውም እንደሚጨምር ገልጿል። የመኝታ፣ ውሃ፣ መብራት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ሁሉ እንደተሟሉ ጠቅሷል።

የአትሌትነት ህይወት በጣም አድካሚ መኾኑን የጠቀሰው አትሌቱ የተገኘውን ተበልቶ እና ተጠጥቶ እንዲሁም የተገኘውን ሥራ ተሠርቶ የሚኖርበት ሳይኾን ራስን ጠብቆ የሚኖርበት መኾኑን ገልጿል። ስለኾነም የአካል ጉዳትን ጨምሮ የሚገጥሙ ችግሮችን ተቋቁሞ ለውጤት መብቃት እንደሚገባ መክሯል።
ወደ ማሠልጠኛ ማዕከል ከመግባቱ በፊትም ለስፖርቱ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራ እንደነበር የተናገረው በቃሉ በዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስን አጥንቶ የአትሌቲክስ ሥራውን በእውቀት ማዳበር እንደሚፈልግ ገልጿል።

አብዛኞቹ ወላጆች ልጆቻቸው የመንግሥት ሠራተኛ እንዲኾኑላቸው ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን በአትሌቲክሱ ዘርፍም ጠንክሮ ሠርቶ ውጤታማ መኾን እንደሚቻል ማሳየት ይገባል ነው የሚለው። ወላጆቹም ውጤታማነቱን እያዩ በርታ በማለት እየደገፉት ነው። በተለይ ታላቅ ወንድሙ እያበረታታው እና እየደገፈው መኾኑን ተናግሯል።

የተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ እና አሠልጣኝ ሙሐመድ አለባቸው በማዕከሉ 57 አትሌቶች እየሠለጠኑ እንደሚገኙ እና ከሜዳ ተግባር እስከ ረጅም ርቀት ድረስም ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑን ጠቅሰዋል። ውርወራ እና ዝላይም በማዕከሉ ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ከፕሮጀክቶች የሚመጡትን ታዳጊዎች ተቀብሎ እያሳደገ ለክለቦች የሚመግብ እና ታዳጊዎች የሚያድጉበት መኾኑን ገልጸዋል። በርዝመት እና በሱሉስ ዝላይ አራት አትሌቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ተንታ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል በወሎ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ የሚደረግለት ሲኾን በርካታ አቅርቦትም እንዳለው ገልጸዋል። ለአትሌቶቹ የሚደረገው የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አበረታች ስለመኾኑም ተናግረዋል። ለቀለብም ኾነ ለኪስ የሚሰጠው ክፍያም ጥሩ መኾኑን ገልጸዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለሠልጣኝ አትሌቶቹ እንደየ ደረጃቸው ምግብን ጨምሮ ከ5 ሺህ 500 እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ እንደሚከፍል ነው የጠቀሱት።

ማሠልጠኛ ማዕከሉ በ2008 ዓ.ም በተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ፕሮጀክትነት ተጀምሮ በ2013 ዓ.ም ደግሞ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ተረክቦ እያስተዳደረው እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። ማዕከሉ በአራት ዓመታት ውስጥ ውጤታማ አትሌቶችን እያፈራ መኾኑን የጠቀሱት አሠልጣኝ ሙሐመድ በዓለም ሻምፒዮና እና በአህጉር ደረጃ የሚወዳደሩ አትሌቶች መፈራታቸውን ገልጸዋል።

በ2014 ዓ.ም ብራዚል በተደረገ የዓለም የወጣቶች ሻምፒዮና ከ20 ዓመት በታች ማዕከሉ ያፈራት አትሌት በ3 ሺህ ሜትር 2ኛ ወጥታለች። በ2015 ዓ.ም በአውስትራሊያው የዓለም ሀገር አቋራጭ በ6 እና 8 ኪሎ ሜትር ማሠልጠኛ ማዕከሉን የወከሉ አንድ ሴት እና አንድ ወንድ አትሌት ተሳትፈዋል። ለቱኒዚያው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና ደግሞ ሦስት የማዕከሉ አትሌቶች በ3 ሺህ ሜትር ተወዳድረው አንድ ወርቅ ማግኘት ሲቻል ሌሎች ደግሞ 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል።

ማሠልጠኛ ማዕከሉ ዘመናዊ የመሮጫ ትራክ እና ጂምናዚየም ቢሟላለት ከዚህ በላይ ውጤታማ እንደሚኾን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። ትጥቅ፣ አልባሳት፣ ሙያዊ ድጋፍ እና የሥነ ልቦና ትምህርትም አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል። የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ዋና አሠልጣኝ አማረ ሙጬ የመጀመሪያ ዲግሪውን በስፖርት ሳይንስ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በአትሌቲክስ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ተምሯል። ከዓለም አቀፍ አማተር አትሌቲክስ ማኅበርም ሁለተኛ ደረጃ የአሠልጣኝነት ሰርተፍኬት አለው።

ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች እየሠራ ሲኾን አሁን ላይ የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል አሠልጣኝ ነው። አሠልጣኝ አማረ በአማራ ክልል የአትሌቲክስ ስፖርት ከአምስት ዓመታት በፊት በጠንካራ ንቅናቄ ላይ እንደነበር እና በየቦታው በተሠራ ሥራ ከ20 ዓመት በታች ብቁ አትሌቶችን ማፍራት ተጀምሮ እንደነበር በመግለጽ አሁን ላይ መቀዛቀዝ እንዳለ ገልጿል።

በቀጣይ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ንቅናቄ በመፍጠር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁሟል። አትሌቲክሱ ላይ በመተጋገዝ ከተሠራ አትሌቶችን ወደ ሌላ ቦታ ከመፍለስ በማዳን ስፖርቱንም ማሳደግ እንደሚቻል ነው አሠልጣኝ አማረ ያመላከተው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here