12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሐዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

0
202

ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ውድድሩ ከሰኔ 25/2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም እንደሚከናወን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

በውድድሩ አጠቃላይ 971 አትሌቶች በተለያዩ የሜዳ ላይ ተግባራት ውድድር ይሳታፋሉ።

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ክፍል ኀላፊ አስፋው ዳኜ፤ የውድድሩ ዋና ዓላማ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እና በሀገሪቱ ላሉ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር መኾኑን ገልጸዋል።

ሚኒማ የሚያሟሉ እና ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተወዳዳሪዎችም ነሐሴ/2016 ዓ.ም ላይ በፔሩ ሊማ ከተማ ለሚደረገው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ ሀገራቸውን ወክለው ይሳተፋሉ ብለዋል።

የዕድሜ ተገቢነትን በተመለከተም ተወዳዳሪዎች ዕድሜን በሚመጥን መልኩ እንዲሳተፉ ለክልል ተቋማት አቅጣጫ ቢቀመጥላቸውም በታሰበው ደረጃ ባለመሳካቱ ፌዴሬሽኑ ወደ ምርመራ መግባቱን ነው የገለጹት።

ከውድድሩም በፊት የዕድሜ ተገቢነትን ለማረጋገጥ የኤም አር አይ ምርመራ እንደሚያደረግ እና ተመርምረው የሚያልፉ ተወዳዳሪዎች ብቻ በውድድሩ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ከዕድሜ እርከኑ በላይ ኾኖ ውድድሩን ለመሳተፍ በመጣ ተወዳዳሪ ላይ ግን የማያዳግም እርምጃ ፌዴሬሽኑ እንደሚወሰድ ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል 40ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር በሐዋሳ ከተማ ሰኔ 30 /2016 ዓ.ም እንደሚከናወን ተገልጿል።

ለውድድሩም ሽልማት ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተዘጋጀ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here