የአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ጀግኖች!

0
333

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ዋንጫ ከመጀመሪያው ውድድሩ እስከ አሁኑ የጀርመኑ ድግስ በየጊዜው ድንቅ ተጫዋቾችን አሳይቷል። እነዚህ ተጫዋቾች በግል በውድድሩ ያሳዩት ብቃት እና ለብሔራዊ ቡድናቸው ስኬት የነበራቸው ድርሻ ውድድሩ ሲነሳ ስማቸው ቀድሞ እንዲታወስ አድርጓቸዋል።

ፕላስ ስፖርት የተሰኘ የመረጃ ምንጭ ከአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜ ምርጦች ውስጥ ፈረንሳዊ ሚሸል ፕላቲኒ አንዱ ነው ይላል። ፕላቲኒ በፈረንሳይ እግር ኳስ የተሻለ ዝና ካተረፉ የቀደሙ ኮከቦች አንዱ ነው። በ1970ዎቹ መጨረሻ እና 80ዎቹ መጀመሪያ በዓለም እግር ኳስ ዝናቸው ጫፍ ከደረሰ ኮከቦች ውስም ፕላቲኒ አንዱ ነበር።

ፈረንሳይ የ1984ቱ የአውሮፓ ዋንጫ አዘጋጅ ነበረች። በዚህ ውድድር ፕላቲኒ ድንቅ ሆኖ ነበር። በአምስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦችንም አስቆጥሯል። ይህም በአንድ የአውሮፓ ዋንጫ ብዙ ግብ በማስቆጠር እስካሁንም ድረስ ብቸኛ ተጫዋች አድርጎታል። ፈረንሳይም በኮከቧ ታግዛ የ1984ቱን የዋንጫ ባለቤት መኾን ችላለች።

ሌላኛው ፈረንሳዊ ዚነዲን ዚዳን ከአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ምርጦች አንዱ። የዘር ሀረጉ ከአፍሪካ የሚመዘነው ዚዳን በእግር ኳስ ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ ስለመኾኑ ብዙዎችን ያስማማል። በእኤአ 2000 ላይ የተካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ ዚዳን ዓለምን ያስጨበጨበበት ነበር። ከምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ እስከ ፍጻሜ ድንቅ የነበረው ዚዙ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ነበር። ፈረንሳይም በውድድሩ ታሪክ ሁለተኛ ዋንጫዋን እንድታነሳ ለነበረው ውለታ አሁንም ድረስ በስሙ ይዘመራል።

አንድሬስ ኢኔስታ የስፔን ወርቃማ ትውልድ አካል። በአውሮፓ ዋንጫ ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ ነው። በባርሴሎና የሚያስቀና የእግር ኳስ ባለቤቱ ኢኔስታ በስፔን ብሔራዊ ቡድንም በኩራት የሚነገር ታሪክ ጽፏል። ከሀገሩ ጋር በ2008 እና በ2012 የአውሮፓ ዋንጫን አንስቷል። በእነዚህ ጊዚያት የነበረው ድንቅ ብቃትም በአውሮፓ ዋንጫ ከታዩ ምርጦች መካከል እንዳደረገው ብሊቸር ሪፖርት አስነብቧል።

ሆላንድ በታሪኳ የአውሮፓ ዋንጫን አንድ ጊዜ አንስታለች። ጊዜው 1988 ተመስጋኙ ደግሞ ማርኮ ቫንባስተን ነው። ቫንባስተን በወቅቱ ምርጥ ብቃቱን ያሳየ ሲኾን አምስት ግቦችን በማስቆጠር ሀገሩን የዋንጫ ባለቤት አድርጓል። በፍጻሜው የያኔዋ ሶቬት ሕብረት ላይ ያስቆጠራት ግብ በእግር ኳስ ከታዩ ምርጥ ግቦች አንዷ ተደርጋ ትዘከራለች።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ መሥራቱን ቀጥሏል። በብዙ የአውሮፓ ዋንጫዎች በመሳተፍ፣ በውድድሩ ታሪክ ብዙ ግብ በማስቆጠር፣ በብዙ ጨዋታዎች በመሰለፍ የሚሉ ክብረወሰኖች ባለቤት ነው። በ2016 የአውሮፓ ዋንጫን ከሀገሩ ጋር ዋንጫውን ከፍ አድርጓል። ብርቱው ሰው እድሜው ለአራት አስር ተቃርቦም ሌላ ክብረወሰን ለመጨመር እየተጋ ነው። በዩሮ ስፖርት መረጃ መሠረት ከአውሮፓ ምርጦች መካከል ቀዳሚውም ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው።

ስፔናዊ ዣቪ ሄርናንዴዝ፣ ፖርቱጋላዊ ሊዊስ ፊጎ፣ ጣሊያናዊ ጃንልጅ ቡፎን ሌሎች የአውሮፓ ዋንጫ ምርጦች ናቸው። የሶቬት ሕብረቱ ሊቭ ያሽን፣ የግሪኩ ቴዎድሮስ ዛጋራኪስ፣ ጀርመናዊ ማቲያስ ሳመርም በአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ምርጥ የሚያስብል ታሪክ ጽፈዋል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here