ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በድምቀት የቀጠለው የአውሮፓ ዋንጫ በምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ሦስት ጨዋታዎችን ያከናውናል። ጨዋታዎቹም ጀርመን ከሀንጋሪ እና ስኮትላንድ ከስውዘርላንድ እንዲሁም ክሮሽያ ከአልባንያ የሚገናኙባቸው ናቸው። አዘጋጇ ጀርመን በመክፈቻ ጨዋታ ስኮትላንድን 5 ለ 1 በማሸነፍ የተሻለ ተነሳሽነት ላይ ትገኛለች። ዛሬ ሦስት ነጥብ ማሳካት ከቻለችም ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏ ይረጋገጣል።
ሀንጋሪ በበኩሏ በመጀመሪያ ጨዋታ በስውዘርላንድ ተሸንፋለች። ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ተስፋዋን ላለማጣትም ዛሬ ነጥብ ለማግኘት ትጫወታለች። ስኮትላንድ በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ እስካሁን ብዙ ግብ ያስተናገደ ቡድን ነው። ዛሬ ስውዘርላንድን ሲገጥምም ቡድኑ ከአስከፊው ሽንፈት ለማገገም እና በውድድሩ ለመቆየት በማሰብ ነው።
ስውዘርላንዶችም ጨዋታውን አሸንፈው ከጠንካራዋ ጀርመን ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ወደቀጣዩ ዙር ማለፍን ግብ አድርገው ይጫወታሉ። ጀርመን ከሀንጋሪ ምሽት አንድ ሰዓት፣ ስኮትላንድ ከስውዘርላንድ ደግሞ ምሽት አራት ሰዓት እንደሚጫወቱ የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!