ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የአውሮፓ ዋንጫ ጀርመን ስኮትላንድን በአምስት ግቦች ባሳቀቀችበት ጨዋታ ተጀምሮ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎችን አጠናቋል። በምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ቤልጀም ሽንፈት ማስተናገዷ፣ የእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና የመሳሰሉ ትልልቅ ብሔራዊ ቡድኖች አሳማኝ ብቃት አለማሳየት ትልቅ ጉዳዮች ናቸው።
በተጫዋቾች በኩል ወደ አውሮፓ ዋንጫው ሲመጡ ብዙ ከተወራላቸው ታላላቅ ተጫዋቾች /በአንድ ጨዋታ መገምገም ልክ ባይኾንም/ ወጣት ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድናቸው ሁነኛ ኾነው ታይተዋል። አዘጋጇ ጀርመን ስኮትላንድን 5 ለ 1 በኾነ ውጤት ማሸነፏ ይታወሳል። ጀርመን በዚህን ያህል ግብ ስትንበሸበሽ ታዳጊው ጀማል ሙሴላ ድንቅ ብቃት አሳይቷል። ሙሴላ ግብ ከማስቆጠር በተጨማሪ ለስኮትላንድ ተከላካዮች ስቃይ ኾኖ ባመሸበት ጨዋታ የጨዋታው ኮከብ መባሉ ይታወሳል።
እንግሊዝ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ በሰርቪያ ብዙ ተፈትናለች። እንግሊዛዊያን ብዙ እያወሩለት የሚገኘው የዘንድሮው ስብስብ በተባለው ልክም በጨዋታው አሳማኝ ኾኖ አልተገኘም። ነገርግን ብቸኛ የማሸነፊያ ግብ ያስቆጠረው ጁዲ ቤሊንግሀም ጥሩ ብቃት አሳይቷል። ተጫዋቹ የጨዋታው ኮከብም ነበር።
ስፔን በአውሮፓ ዋንጫው በወጣቶች የተዋቀረ ቡድን ይዛ ቀርባለች። ከጠንካራዋ ክሮሽያ ጋር ያደረገችውን የምድብ ጨዋታም በአሳማኝ ብቃት አሸንፋለች። በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪው ደግሞ የ16 ዓመቱ ላሚን ያማል ነው። ታዳጊው በጨዋታው ግብ የኾነ ኳስ በማቀበል እና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንቅስቃሴ በማድረግ ድንቅ ብቃት ማሳየቱን የዩሮ ኒውስ መረጃ ያሳያል።
ተርኪየ ጆርጅያን ባሸነፈችበት ጨዋታ ታዳጊው አርዳ ጉለር አስገራሚ ብቃት አሳይቷል። የሪያል ማድሪዱ ታዳጊ ኮከብ በቤርናባው የተሻለ የመጫወት እድል ቢሰጠው ምን ይሠራ ይኾን እያስባለ ነው። ጉለር ሀገሩ ጆርጅያን 3 ለ 1 በረታችበት ጨዋታ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል። በጨዋታው የነበረው አጠቃላይ እንቅስቃሴም የጨዋታው ኮከብ ተብሎ እንዲመረጥ አድርጎታል።
የሮናልዶ ሀገር ፖርቱጋል ከቼክ ጋር የነበራት ጨዋታ እልህ አስጨራሽ ነበር። የኮከቦቹ ሀገር የጨዋታ ብልጫዋን ወደ ግብ ለመቀየር ተቸግራ ነበር። የማታ ማታ ከመመራት ተነስታ ጣፋጭ ድል ስታስመዘግብም የታዳጊው ፍራንሲስኮ ኮንሴ ሳኦዎ የመጨረሻ ደቂቃ ምትሀት አስፈልጓታል። የአውሮፓ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይቀጥላሉ። በውድድሩ የእስካሁን ጉዞ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ይልቅ ወጣቶች ደምቀው ታይተዋል። ውድድሩ ገና እየተጀመረ በመኾኑ በቀጣይ የትኞቹ ተጫዋቾች ጎልተው ይወጣሉ የሚለውም ይጠበቃል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!