ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የሩዋንዳው አማሆሮ ብሔራዊ ስታዲየም ለመጀመሪያ ጊዜ ተገንብቶ የተጠናቀቀው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1986 ነበር፡፡ “አማሆሮ” ማለት “ሰላም” ማለት ሲኾን ይህ ስታዲየም ለዓመታት በርካታ ጨዋታዎችን ቢያስተናገድም ተመልካች የመያዝ አቅሙ አነስተኛ ስለነበር እንደገና 25ሺህ ተመልካች እንዲይዝ ተደርጎ በ2011 እድሳት ተደርጎለታል፡፡ ይሁንና ስታዲየሙ በድጋሜ ሲታደስ የፊፋንም ኾነ የካፍን ምክረ ሐሳብ ሳይጠየቅ ነበርና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንዳይችል በሁለቱም አካላት ታግዷል፡፡
የሩዋንዳ መንግሥትም ስታዲየሙን በካፍ እና በፊፋ ሙያተኞች ካስጎበኘ በኋላ “በምን መልኩ ይታደስ? ፤ምን ምን ኹኔታዎችንስ ይጨመሩበት?” ሲል ጠየቀ፡፡ ካፍ እና ፊፋም አስፈላጊውን ምክረ ሐሳብ ለሩዋንዳ መንግሥት ሰጡ፡፡ መንግሥትም በተባለው ልክ ለመሥራት ወሰነ፡፡
እ.ኤ.አ በነሀሴ 2022 አጋማሽ 170 ሚሊዮን ዶላር በጅቶ ወደ ሥራ ገባ፡፡ ግንባታውንም የተርክዬው “ሱማ” ኩባንያ እና የሩዋንዳው “ሬያል ኮንትራክተሮች” ከ25ሺህ መቀመጫ ወደ 45ሺህ 508 መቀመጫ አሳድገው በመሥራት እና በ2024 አጋማሽ ላይ አጠናቀው ለማስረከብ በጋራ ተስማምተው ሥራውን ጀመሩ፡፡
በውሉ መሠረትም የአማሆሮ ስታዲየም የእግር ኳስ ሜዳ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ሳር ተተከለለት፡፡ አማሆሮ የመሮጫ መምም ተነጥፎለታል፡፡ የፓራሊምፒክ ጂምናዚየምም እንዲሁ፡፡ አማሆሮ ብሔራዊ ስታዲየም ዓለም አቀፍ የእጅ እና የመረብ (ቮሊቦል) ኳስ ጨዋታዎችን እንዲያስተነግድ ኾኖ ነው የታደሰው፡፡ በመኾኑም ስታዲየሙ ከሰሞኑ ሁሉንም ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ያሟላ እንደኾነ ተነግሯል፡፡
በስታዲየሙ በውስጥ በኩል እና በቅጥር ግቢው ዘመናዊ የደህንነት ቁጥጥር ቴክኖሎጂዎች ተገጥሞለታል፡፡ የዘመኑ የሚዲያ ማሳራጫ ቦታዎች እና ቁሳቁስም አለው ነው የተባለው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ትኬት መቁረጫዎች ፣ የአትሌቲክስ አውቶማቲክ የውጤት መከታተያ ሥርዓቶች እና ሌሎችም ግብዓቶች ተሟልተውለታል ነው የተባለው፡፡
ካፍ ሰኔ 13 ቀን 2024 በጻፈው ደብዳቤ የአማሆሮ ስታዲየም በዘመናዊ ረገድ ‘በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ካሉት ምርጥ ስታዲሞች አንዱ’ በማለትም አሞካሽቶታል፡፡ የዓለም እግር ኳስ አሥተዳዳሪ አካል (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የአማሆሮ ስታዲየምን ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች እንዲደረግበት ከሰሞኑ አጽድቀውታል ሲል አፍሪካ ቶፕ ስፖርትስ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
የሩዋንዳ የስፖርት ሚኒስትር አውሮር ሚሞሳ እንዳሉት ካፍ እና ፊፋ ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች እንዲደረግበት በመፍቀዳቸው መንግሥት መደሰቱን ገልጸው” ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ይመረቃል” ብለዋል፡፡ የባሕር ዳሩ ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ጨምሮ በርካታ ጅምር ስታዲየሞች በሀገራችን ይገኛሉ። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም አጉራዊ ውድድሮችን ለማድረግ የተውሶ ሜዳ ፍለጋ እየተንከራተተ ነው። በተለይ የባሕር ዳሩ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደ ሩዋንዳው አማሆሮ መቼ የፊፋን እና ካፍን ፍቃድ ያገኝ ይኾን? የሚለው በብዙ ይናፈቃል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!