ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዶሪቫል ሲልቬስትሬ ጁኒየር አዲሱ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሊኾኑ ነው። ሥራቸውን ለመጀመርም የሚያሠለጥኑትን የሳኦ ፓውሎ ክለብን ተሰናብተው ሪዮ ዴ ጄኒሮ መግባታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ብራዚል የብሔራ ቡድኗን ጊዜያዊ አሠልጣኝ ፈርናንዶ ዲኒዝን ከሰሞኑ ማሰናበቷን ተከትሎ የ61 ዓመቱ ዶሪቫል ሲልቬስትሬ ጁኒየር ብሄራዊ ቡድኑን እንዲመሩ እድሉ ሰጥታቸዋለች ነው የተባለው፡፡ ስለሆነም አዲሱ አሠልጣኝ ሲያሰሠጥኑት የነበረውን የሳኦ ፓውሎን ቡድን በይፋ ተሰናብተው መሄዳቸውን ክለቡ በኤክስ ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡
ዶሪቫል ጁኒየር የአሠልጣኝነት ሥራ የጀመሩት እንደ አውሮፖውያኑ አቆጣጠር በ2002 እንደነበር ሮይተርስ አስታውሶ ሰውየው በክለብ ደረጃ 25 ቡድኖችን ማሠልጠን ችለዋል ብሏል፡፡
አሠልጣኙ በተለይ በ2010 በሳንቶስ ክለብ ቆይታቸው እንደ ኔይማር እና ፓውሎ ሄንሪኬ ፣ጋንሶ ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን እያሠለጠኑ የብራዚል ቡድን ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግብ አድርገዋል ነው የተባለው፡፡
ዶሪቫል ጁኒየር፤በ2022 በሀገረ ብራዚል የውስጥ የውድድር ዘመንም ከፍላሜንጎ ቡድን ጋር መልካም ጊዜን አሳልፈዋል፡፡ በ2023 ደግሞ የሳኦ ፓውሎን ቡድንን አሠልጥነው የኮፓ ደ ብራዚል ዋንጫን በማሸነፍ ባለ ስኬት ለመኾን በቅተዋል ሲል ሱፐርስፖርት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ዶሪቫል ጁኒየር ከ1976 እስከ1999 ድረስ በተለያዩ ቡድኖች በተከላካይ አማካይ ቦታ በተጫዋችነት ማሳፋቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
የዓለም ዋንጫ በ2026 በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ይካሄዳል። የብራዚል ብሔራዊ ቡድንም ስድስት ጨዋታዎችን አድርጎ በሁለቱ ብቻ አሸንፎ በሦስቱ ተሸንፎ እንዲሁም በአንዱ አቻ በመውጣት ከምድቡ በስድስተኛ ደረጃን ይዞ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ አይዘነጋም፡፡ በመኾኑም አሠልጣኙ ይህን ቡድን ለዓለም ዋንጫ እንዲያደርሱት ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!