ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ዴንማርካዊው ክርስቲያን ኤሪክሰን በሆላንዱ አያክስ አመስተርዳም ክለብ ሲጫወት ሦስት የኤርዲቪዝን (የሆላንድ ክለቦች ዋንጫ) አሳክቷል፡፡ በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2013 የእንግሊዙን ቶተንሃም ሆትስፐርን ተቀላቅሎም ሁለት ጊዜ የሆትስፐር የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡ ከሆትስፐር ጋር በ2019 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚም ኾኗል፡፡
በ2020 ወደ ጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ያቀናው ዴንማርካዊው የመሐል ሞተር ከኢንተር ጋር በመኾንም የጣሊያኑን ሴሪ ኤ ዋንጫ አሳክቷል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት የአውሮፓ ሀገራት ዋንጫ ላይ ሀገሩ ዴንማርክን ወክሎ በመጫወት ላይ እያለ በድንገተኛ የልብ ሕመም ሜዳ ውስጥ ተዝለፍልፎ ወድቋል፡፡
በዚሁ ድንገተኛ አደጋ የዳኒሽ እግር ኳስ ተጨዋቾች ብቻ ሳይኾኑ የዓለም እግር ኳስ ወዳጆች ሁሉ በጣሙን አዝነዋል፡፡ ያም ኾኖ ግን ለክርስቲያን ኤሪክሰን በተደረገለት አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ከሞት ደጃፍ ወደ ሕይዎት ተመልሷል፡፡ የመተንፈሻ ችግር ያለባቸውን ተጨዋቾች ወደ ሜዳ ያለማስገባት ሕግ ያላት ጣሊያን ኤሪክሰን ከሕመሙ ከዳነ በኋላ በኢንተር ሚላን እንዲጫወት አልፈቀዱለትም፡፡
ከኢንተሮች የጨዋታ ፈቃድ ያጣው ኤሪክሰን በእንግሊዙ ብሬንትፎርድ የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚሁ ውጤታማነቱ ምክንያትም የእንግሊዙን ኃያል ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድን መቀላቀል ችሏል የሚለው የቢቢሲ እና የስካይ ስፖርት ዘገባ አሁንም ድረስ በማንቸስተር ዩናይትድ የመሐል ሜዳ ተጨዋች ኾኖ እንደቀጠለም ይጠቀሳል፡፡
ጀርመን ባዘጋጀችው የአውሮፓ ዋንጫ ላይ ሀገሩ ዴንማርክን ወክሎ በ33 ዓመቱ እየተጫወተ የሚገኘው ኤሪክሰን ትላንት ምሽት ሀገሩ ዴንማርክ ከስሎቬኒያ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ግብ አስቆጥሮ መሪ ቢያደርጋትም ዘግይቶ በተቆጠረባቸው ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ ከሞት አፋፍ የተመለሰው ዴንማርካዊው የመሐል ሞተርም ለሀገሩ አንድ ነጥብ በማስገኘት ለብዙ ወጣቶች የተስፋ ተምሳሌት ኾኖ ቀጥሏል፡፡ ዴንማርክ በምድብ ሦስት ከሰርቢያ፣ ስሎቬኒያ እና እንግሊዝ ጋር መደልደሏ ይታወቃል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!