ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የቮሊቦል ጨዋታ አነስተኛ በጀት የሚጠይቅ ነው። አንጻራዊ በኾነ ሁኔታ እንደ እግር፣ እጅ እና ቅርጫት ኳስ ሰፋ ያለ ሜዳ አያስፈልገውም። በየመሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ እንዲሁም በየአካባቢው በትንሽ ሥፍራ ለማካሄድ የተመቸ ነው። በባሕር ዳር ከተማ ከ1980ዎቹ ቮሊቮል በስፋት ይዘወተር ነበር። ጨዋታውን በውስን ቦታ እና በቀላል ወጭ ማከናዎን በመቻሉም መምህራን ሳይቀሩ በየትምህርት ቤቶቻቸው ያዘወትሩት ነበር።
በአማራ ክልል የቮሊ ቦል ጨዋታ በ1970 ዎቹ እንደ እንጉዳይ የፈካበት ወቅት እንደ ነበር የጽሑፍ እና የሰው መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚያ ትውልድ ውድድሮች በቀበሌ፣ በወርዳ፣ በአውራጃ፣ በክፍለ ሀገር እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከናወኑ ነበር። በወቅቱ አንድ የእግር ኳስ ቡድን ያቋቋመ መሥሪያ ቤት የግድ በሁለቱም ጾታዎች የቮሊቦል ቡድን እንዲያቋቁም በሕግ ይገደድ ነበር ተብሏል።
“ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ” ነውና ብሂሉ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ኤልያስ መኮንን በመላ ሀገሪቱ ቅዳሜ እና እሑድ በየአካባቢው መርሐ ግብር የወጣለት የሞቀ የቮሊ ቦል ጨዋታ ይካሄድ ነበር በማለት ያስታውሳሉ። አሁን ግን ይላሉ መምህሩ የቮሊቦል ጨዋታ በአማራ ክልል በጣም ተዳክሟል ከማለት በላይ ነው አሉን።
አብነት ሲጠቅሱም ባሕር ዳርን በሚያክል ሰፊ እና ዘመናዊ ከተማ ከባሕር ዳር ከነማ ውጭ የቮሊ ቦል ቡድን አለመኖሩን ያነሳሉ። ( “ጣና ባሕር ዳር ” የወንዶች ቮሊ ቦል ቡድን ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ መኾኑን ልብ ይሏል) እንደ መምህር ኤልያስ በክልሉ የጣና ባሕር ዳር “ተፎካካሪ ቡድን እና በየከተማዎቹ የታዳጊ የቮሊ ቦል ፕሮጀክቶች አለመኖር ለዘርፉ መዳከም ምሥክር ነው ባይ ናቸው።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞው የቮሊ ቦል ተጫዋች ሰፊ ገበየሁ በበኩላቸው ቀደም ባሉት ጊዚያት በአማራ ክልል የቮሊ ቦል ስፖርት ጠንካራ ቡድኖች እንደነበሩት አነሱ። ውድድሮችም ሳይቆራረጡ ይደረጉ እንደ ነበር ተናግዋል። እስከ 1990ዎች ጨዋታዎች በፍላጎት እና በፍቅር ይደረጉ ነበር። የተመልካቹ ቁጥርም በርካታ ነበር። ስለኾነም የቮሊ ቦል ስፖርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር” ሲሉ አቶ ሰፊ አስታውሰዋል።
ታዲያ አሁን ቮሊቦል ጨዋታ ለምን ተዳከመ? በርካታ የቮሊ ቦል ቡድኖች አለመኖራቸው እና የታዳጊ ፕሮጀክቶች በስፋት አለመከፈታቸው በዘርፉ ተተኪዎች እንዳይወጡ እና ስፖርቱ መዳከሙን አቶ ሰፊ በምክኒያት አንስተዋል። የአማራ ክልል ቮሊ ቦል ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በላይ አበጀ የቮሊ ቦል ስፖርት ተዳክሟል መባሉን አምነዋል። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ቮሊ ቦል ፌዴሬሽን በክልሉ የቮሊ ቦል ስፖርት የቀደመ ስም እና ዝናውን ለመመለስ ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የቮሊ ቦል ሊግ አስጀምሯል ብለዋል። በዚህ መድረክም ከ17 ክለቦች በላይ መሳተፋቸውን አስታውሰዋል።
“ወቅታዊው የሰላም እጦት ወደ ኋላ መለሰው እንጅ” ብለዋል። ፌዴሬሽኑ በሁሉም የአማራ ክልል ቦታዎች በዘርፉ አቅም እንዳለ ቢረዳም እስካሁን ግን በተገቢው ልክ አለመሥራቱን አንስተዋል። የሥልጠና ቦታዎችን በመለየት እና በማጠናከር፣ አሠልጣኞችን በማብቃት እና ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ በመሥራት በኩል የሚታዩ ክፍተቶች መኾናቸውንም የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አብራርተዋል። ይህ በዚህ እንዳለ በችግር ውስጥ ኾኖም የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደርን የወከለው የባንጃ የቮሊ ቦል ቡድን በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የኢትዮጵያ የክልል ሻምፒዮና አሸናፊ ኾኗል።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የቮሊ ቦል ጨዋታ እንደ እግር ኳስ ሁሉ በሥፋት የሚዘወተር ጨዋታ ነው። የቀድሞው የጎጃም ክፍለ ሀገር ዝነኛ የቮሊ ቦል ተጫዋች ሰማነህ ዘለቀ (አፈሩ ይቅለላቸውና ) እንደ ወርቅ ነጥረው የወጡት ከአዊ መኾኑን ልብ ይሏል።
የባንጃ ቡድን አዲስ አበባ ላይ በነበረው ጨዋታ በምድብ ሁለት ተደልድሎ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍ የምድቡ መሪ ኾኖ ማጠናቀቁ የሚታዎስ ነው። በፍጻሜው ጨዋታም የኦሮሚያውን ግሎባል ኮሌጅን 3 ለ 1 በመርታት ነው ሻምፒዮን የኾነው። በመኾኑም ቡድኑ በ2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ መኾኑን አረጋግጧል።
አሠልጣኙ ሰውበሰው ታደሰ ቡድኑ በውድድር ዘመኑ በስፖርተኞች ብርቱ ጥረት እና በስፖርት ቤተሰቦች ድጋፍ ለስኬት መብቃቱን ተናግረዋል። አሠልጣኙ አያይዘውም ቡድኑ በቀጣይ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ እንደመኾኑ ከፍተኛ እገዛ እና ድጋፍ ይሻል ነው ያሉት። የባንጃ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ እና የስፖርት ምክር ቤት ሠብሣቢ ሞላ ወሌ ቡድኑ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለውጤት በመብቃቱ አመሥግነዋል። 2017 ዓ.ም ለሚኖረው የፕሪሚየር ሊግ ተሳትፎው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግለትም አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ምክትል ኀላፊ ጋሻው ተቀባ በበኩላቸው የባንጃ ቮሊቦል ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት እጅግ የሚያስደስት ነው ብለዋል። በቀጣይ የክልሉን የቮሊ ቦል ስፖርት ለማነቃቃት የሚረዳ ነውም ብለዋል። የባንጃ የቮሊ ቦል ቡድን በችግር ውስጥ ጉዞውን ቢያደርግም በተነሳሽነት፣ በማሊያ ፍቅር እና ተስፋ፣ በቁርጠኝነት እና ቁጭት ጠንክሮ በመሥራቱ ለውጤት በቅቷል። ይህ ትጋቱ ደግሞ በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ለተሰለፉ ስፖርተኞች እና ቡድኖች አስተማሪ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!