የስፔናውያን አሠልጣኞች ስኬት!

0
189

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተጠናቀቀው የ2023/24 የውድድር ዘመን ስፔናውያን አሠልጣኞች በአውሮፓ ትልቅ ተጽዕኖ የፈጠሩበት ጊዜ እንደነበር ሮይተርስ አስነብቧል። በቁጥር ጥቂት የማይባሉ ስፔናውያን የእግር ኳስ አሠልጣኞች ስኬታማ የውድድር ጊዜ ማሳለፋቸውን ነው መረጀው ያስነበበው።

በዘገበው የተጠቀሱት አሠልጣኞች የቀድሞ የአማካይ ክፍል ተጫዋቾች መሆናቸው ጨዋታን የመረዳት ትልቅ አቅም እንዲኖራቸው እና የፈጠራ አቅማቸው ከፍ እንዲል እንዳገዛቸው ዘገባው ያስረዳል። አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በዓለማችን ከሚገኙ ምርጥ የእግር ኳስ አሠልጣኞች መካከል በቀዳሚነት ይቀመጣል። የካታለኑ ክለብ የሚታወቅበትን የቲኪ ታካ እግር ኳስ ፍልስፍና በኑካምፕ ማስቀጠል ችሏል። ስፔናዊው አሠልጣኝ በባየርን ሙኒክ እና ማንቸስተር ሲቲም ከመልካም የእግር ኳስ ፍልስፍና ጋር አስደናቂ ሥራ ሠርቷል። ጓርዲዮላ በርካታ ተከታዮችንም ያፈራ አሠልጣኝ ነው።

ዣቢ አሎንሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ የኾነ ስፔናዊ አሠልጣኝ ነው። የ42 ዓመቱ አሠልጣኝ በተጫዋችነት ዘመኑ ምርጥ ከሚባሉት የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች አንዱ እንደነበርም አይዘነጋም። በአንድ ጨዋታ ከ200 በላይ ቅብብሎችን ካደረጉ ሦስት ተጫዋቾች መካከልም አንዱ ነው። በአንፊልድ ከራፋ ቤኒቴዝ፣ በሳንቲያጎ ቤርናባው ከሆዜ ሞሪንሆ፣ በአሊያንዝ አሬና ከፔፕ ጓርዲዮላ ጋር አብሮ መሥራቱ ደግሞ ይበልጥ የአሠልጣኝነት ሕይወቱ እንዲቃና አድርጎታል።

ዣቢ አሎንሶ በተጠናቀቀው የጀርመን ቡንደስ ሊጋ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባየርን ሊቨርኩሰንን ሻምፒዮን ማድረግ ችሏል። በአውሮፓ መድረክም 51 ጨዋታዎችን በተከታታይ ባለመሸነፍ አዲስ ክብረ ወሰን ጨብጧል። አሠልጣኝ ዣቪ ሄርናንዴዝ በትውልዱ ከነበሩ ድንቅ የመሀል ሜዳ ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበር ይታወሳል። በአሠልጣኝነት ሕይወቱ ደግሞ ምርጥ ብቃቱን ባደገበት ቤት አሳይቷል። ዣቪ በባርሴሎና የሦስት ዓመታት የአሠልጣኝነት ቆይታው በሁለተኛው የሜዳ ክፍል ብልጫ ወስዶ የሚጫወት ቡድን ገንብቶ አሳይቷል። በ2022/23 የውድድር ዘመን ባርሰሎና የላሊጋውን ዋንጫ ማንሳቱ የሚታወስ ነው። ዣቪ በዘንድሮው የውድድር ዓመት መጨረሻ ግን ከባርሴሎና ጋር መለያየቱ ይታወሳል።

አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ስኬታማ ከነበሩት አሠልጣኞች መካከል አንዱ ነው። በኤምሬትስ አዲስ የእግር ኳስ አብዮት በመፍጠር ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል። የቀድሞው የአርሴናል እና የኤቨርተን የመሀል ሜዳ ሞተር በተጫዋችነት ዘመኑም መሪ እና ጥልቅ ዕይታ ያለው መኾኑ ይታወሳል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ በአርሴናል ቤት ውስጥ ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ማራኪ ቡድን ገንብቷል። በወጣቶች የተገነባው ቡድን ዘመናዊ እግር ኳስ የሚጠይቀውን ክህሎት ያሟላ በመኾኑ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር መፎካከር ችሏል።

የ37 ዓመቱ ሴስክ ፋብሪጋዝም በአጭር ጊዜ ስኬታማ ከኾኑ ስፔናውያን አሠልጣኞች ውስጥ ይመደባል። የቀድሞው የአርሴናል፣ የባርሴሎና እና የቼልሲ አማካይ በሞናኮ የነበረውን ቆይታ ካጠናቀቀ በኋላ ነበር በነሐሴ 2022 እንደ አውሮፖውያኑ አቆጣጠር የጣሊያኑን ኮሞን የተቀላቀለው። ከጥቂት ወራት ጊዜ በኋላ ደግሞ ከተጫዋችነት በመገለል የክለቡ አሠልጣኝ በመኾን ኮሞን ወደ ሴሪኤ አሳድጎታል። ፋብሪጋዝ ልክ እንደ ቴሪ ኦነሪ ሁሉ በክለቡ አነስተኛ ድርሻ አለው።

እነዚህ አሠልጣኞች በተጨዋችነት ዘመናቸው አስደናቂ ዕይታ የነበራቸው፣ እግር ኳስን በጥልቀት የሚረዱ እና የሚገነዘቡ ሀሳባዊ ተጨዋቾች መኾናቸው የአሠልጣኝነት ጊዜያቸውንም የተባረከ አድርጎላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ስፔኒያኑን አሠልጣኞች ትንፋሽን የሚያስውጡ ልብን የሚያሞቁ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ቡድኖችን እንዲገነቡ አግዟቸዋል።

ከላይ ከዘረዘርናቸው የመሀል ሜዳ ተጨዋቾች እና አሠልጣኞች ውስጥ ሦስቱ ማለትም ፔፕ ጓርዲዮላ፣ ዣቪ ሄርናንዴዝ እና ሴስክ ፋብሪጋስ ደግሞ የካታላኑ ላሜሲያ አካዳሚ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሦሥቱም ተጨዋቾች በክለባቸው ባርሴሎና እና በስፔን ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ጊዜን እንዳሳለፉም ይታወሳል፡፡
እነዚህን ስፔናዊያን ለአብነት ያህል አነሳን እንጂ የአስቶንቪላው ኡናይ ኤምሪ፣ የፓሪሰን ዥርማው ሉዊስ ኢኔሪኬ፣ የዌስትሀሙ ጁሊያን ሉፕቴጌ፣ የበርንማውዙ አንዶኒ ኢራኦላ እና የጊሮናው ሚሸልም ስኬታማ ስፔናውያን አሠልጣኞች ናቸው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here