ማንቸስተር ሲቲ በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ 14 ተጨዋቾችን በማስመረጥ ቀዳሚ ኾኗል፡፡

0
375

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ሊጀመር ቀናት ቀርተውታል፡፡ ጀርመን ደግሞ ደጋሿ ሀገር ናት፡፡ ከቀናት በኋላ በሚጀምረው የአውሮፓ ዋንጫ አንጋፋ እና ወጣት ተጫዋቾች የሚያሳዩት ብቃት ይጠበቃል፡፡ ጀርመን በደገሰችው ድግስ ዋንጫውን ታስቀረዋለች ወይስ አሳልፋ ትሰጠዋለች የሚለው በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡

በእርግጥ ከጀርመን ይልቅ እንደ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የመሳሰሉ ብሔራዊ ቡድኖች ዋንጫውን ከፍ አድርገው ወደ ሀገራቸው የመመለስ ዕድል እንዳላቸው እየተነገረ ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ዓርብ ሰኔ 14/2024 ተጀምሮ እሑድ ሐምሌ 14/2024 የሚጠናቀቀው የአውሮፓ ዋንጫ በርካታ ከዋክብትን እንደሚያሳይ ይጠበቃል፡፡

በአውሮፓ ዋንጫ የእንግሊዙ ማንቸሰተር ሲቲ 14 ተጫዋቾችን ለሰባት ብሔራዊ ቡድኖች በማስመረጥ ቀዳሚው ቡድን ኾኗል፡፡ እንደ ሚረር ፉት ቦል ዘገባ የጣሊያኑ ኢንተርሚላን እና የስፔኑ ኃያል ቡድን ሪያልማድሪድ ደግሞ እያንዳንዳቸው በተመሳሳይ 13 ተጫዋቾችን ለተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች በማስመረጥ ሁለተኛ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

የፈረንሳዩ ሃብታም ክለብ ፔኤስጂ እና የጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየርንሙኒክ እያንዳንዳቸው 12 ተጫዋቾችን በማስመረጥ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡ አርሰናል ደግሞ 11 ተጫዋቾችን ለጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ አስመርጧል፡፡ የጀርመኑ አር ቢ ላይብዚግ ደግሞ 10 ተጫዋቾችን በማስመረጥ በርካታ ተጫዋቾችን በማስመረጥ ቀዳሚ ከኾኑ ቡድኖች ተርታ ተሰልፏል፡፡

የአውሮፓ ዋንጫ የፊታችን አርብ በአስተናጋጇ ሀገር ጀርመን እና በስኮትላንድ በሚደረገው ጨዋታ ይጀምራል፡፡ የመክፈቻው ጨዋታ 75 ሺህ ደጋፊዎችን በሚይዘው የባየርንሙኒኩ አሊያንዝ አሬና ስታዲዬም ይካሄዳል፡፡ ምሽት 4 ሰዓት ደግሞ ጨዋታው የሚደረግበት ሰዓት ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here