ፈርናንዶ ቶሬስ የአትሌቲኮ ማድሪድ ቢ ቡድን አሠልጣኝ ኾነ፡፡

0
285

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድመው የስፔን ብሔራዊ ቡድን፣ የአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ሊቨርፑል እና ቸልሲ አጥቂ ፈርናንዶ ቶሬስ የአትሌቲኮ ማድሪድ ቢ ቡድን አሠልጣኝ ኾኖ ተሹሟል፡፡ የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ወደዚህ ኀላፊነት ከመምጣቱ በፊት የአትሌትኮ ማድሪድ ከ19 ዓመት በታች ቡድን አሠልጣኝ ነበር፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው የአትሌትኮ ማድድሪድ ቢ ቡድን አሠልጣኝ ኾኖ የተሾመው ቶሬስ “ታላቅ ኀላፊነት ተቀብያለሁ” ብሏል፡፡

ለሀገሩ ስፔን 110 ጨዋታዎችን ያደረገው ቶሬስ በ2010 ከሀገሩ ጋር የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ኾኗል፡፡ ሀገሩ ስፔን በ2008 እና በ2012 የአውሮፓን ዋንጫ ስታሸንፍ ከአሸናፊው ቡድን ጋር ነበር፡፡ ስፔን ዋንጫውን ከፍ ባደረገችባቸው ሁለት የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታዎች በሁለቱም ግብ አስቆጥሯል፡፡

ፈርናንዶ ቶሬስ ከሀገሩ ስፔን ጋር ወርቃማ ጊዜን አሳልፏል፡፡ የአንድ የዓለም ዋንጫ እና የሁለት የአውሮፓ ዋንጫ ባለቤት ነውና፡፡ በአትሌቲኮ ማድሪድ፣ በሊቨርፑል እና በቸልሲ የተጫወተው ቶሬስ ከሊቨርፑል ወደ ቸልሲ ሲዘዋወር በወቅቱ የብሪታኒያ የዝውውር ክብረ ወሰንን በመስበር ነበር፡፡ በወቅቱ ለቶሬስ 50 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ቶሬስ በኤሲሚላንም አጭር ቆይታ እንደነበረው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

እንደ ኢኤስፒኤን ዘገባ ቶሬስ ከቸልሲ ጋር የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግና የኢሮፒያ ሊግ ዋንጫን አሳክቷል፡፡ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋርም የኢሮፓ ሊግ ጨዋታን ከፍ አድርጓል፡፡ ቶሬስ በ2019 ነበር ራሱን ከእግር ኳስ ተጨዋችነት ያገለለው፡፡ በዘመኑ አስፈሪ የፊት መስመር አጥቂ የነበረው ቶሬስ በሚከበርበት የአትሌትኮ ማድሪድ ቤት አሠልጣኝ ኾኗል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here