የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውዱ ብሔራዊ ቡድን ተባለ፡፡

0
418

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጀርመኑ የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ከሚሳተፉ የአውሮፓ ሀገራት መካከል የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውዱ ብሔራዊ ቡድን ተብሏል፡፡ እነ ጁድ ቢሊንግሃም፣ ፊል ፎደን፣ ሀሪ ኬን፣ ዲክላን ራይስ፣ ቡካዮ ሳካ የመሳሰሉ ከዋክብትን የያዘው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውዱን ስብስብ በመያዝ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ እንደ ሚረር ፉትቦል ዘገባ የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ፓውንድ ያወጣል፡፡

የ2018 የዓለም ዋንጫ አሸናፊ እና የ2022 የኳታሩ የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚዋ ፈረንሳይ ከእንግሊዝ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ኪሊያን ሜባፔ፣ አንትዋን ግሪዝማ እና ሌሎች ከዋክብቶችን የያዘው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ዋጋ 1 ነጥብ 04 ቢሊዮን ፓውንድ ነው ተብሏል፡፡ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድኖች በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ከሚሳተፉ ሀገራት ቢሊዮን ፓውንድ በመድረስ የሚስተካከላቸው የለም፡፡

በአንጋፋ እና በወጣት ተጨዋቾች የተሞላው የክርስቲያኖ ሮናልዶ ሀገር ፖርቹጋል ሦስተኛው ውዱ ብሔራዊ ቡድን ተብሏል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ዋጋ 890 ሚሊዮን ፓውንድ ነው ብሏል ሚረር ፉትቦል በዘገባው፡፡ 820 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያወጣ የተገመተው የስፔን ብሔራዊ ቡድን አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር ጀርመን ብሔራዊ ቡድን አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ስብብስ ዋጋ 722 ሚሊዮን ፓውንድ ነው ተብሏል፡፡ ኔዘርላንድ ደግሞ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ የኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ 717 ሚሊዮን ፓውንድ ተገምቷል፡፡

የ2020 የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ሰባተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ወርቃማው ትውልድ ያለ ዋንጫ ክብር ያለፈባት ቤልጂዬም ደግሞ ስምነተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ዴንማርክና ዩክሬን ደግሞ በቅደም ተከተል 9ኛ እና 10ኛ ውድ ብሔራዊ ቡድን ተብለዋል፡፡

በ2018 የሩሲያ የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረችው እና በ2022 የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችው የሉካ ሞዲሪቿ ሀገር ክሮሺያ በ2024 በአውሮፓ ዋንጫ ከሚሳተፉ ውድ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል እስከ አስር በተሰጠው ደረጃ ሳትካተት ቀርታለች፡፡

ውዱ ብሔራዊ ቡድን የተባለው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ዋጋ የጀርመን እና የቤልጄም ብሔራዊ ቡድኖችን ተደምረው ከሚያወጡት ዋጋ ጋር ይተካከላል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here