ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው የ15 ዓመቱ ታዳጊ ዳንኤል ዘውዴ ከትምህርቱ ጎን ለጎን የእግር ኳስ ሥልጠና እየተከታተለ ይገኛል። ታዳጊው እንደሚለው ልምምድ የሚሠሩትም ኾነ ጨዋታዎችን የሚያከናውኑበት ሜዳ ምቹ አይደለም። “እኛ የምንሰለጥንበት ሜዳ የግብ አግዳሚም ኾነ ቋሚ የለውም” የሚለው ዳንኤል አቧራው ዐይናችንን ከመጉዳቱ በተጨማሪ ሜዳው በአግባቡ አፈር ባለመልበሱ እየጎዳን ነው ብሏል።
አለሙ መንግሥቱ ደግሞ የቢቸና ከተማ ነዋሪ እና የስፖርት መምህር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በቢቸና ከተማ የሚገኘው የማዘውተሪያ ሥፍራ ታዳጊዎች ሲጫወቱ ከወደቁ የከፋ አደጋን የሚያስከትል ምቹ ያልሆነ ሜዳ ነው ብለዋል ። መምህሩ ለሥራ በተንቀሳቀሱባቸው በምሥራቅ ጎጃም የተለያዩ ከተሞች በርካታ ወጣቶች የስፖርት ፍቅር እና ዝንባሌ ያላቸው ቢኾንም የማዘውተሪያ ሥፍራዎች እጥረት ግን አላንቀሳቀስ ብሏቸዋል።
አብርሃም ይደግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ የስፖርት መሰረተ ልማት እና ፋሲሊቲ የሦስተኛ ዲግሪ የዚህ ዓመት ተመራቂ ነው። በሰቆጣ ከተማ የታዳጊዎች እግር ኳስ አሠልጣኝ ነበሩ። እንደ እሳቸው ገለጻ በአማራ ክልል የስፖርት መሠረተ ልማትን በተመለከተ ጥናት ሠርተዋል። በጥናታቸው መሠረትም በክልሉ ታዳጊዎች ኳስ ጨዋታዎችን እንዲያደርጉባቸው በሚል በዕቅድ፣ በባለሙያ ድጋፍ እና ምክረ ሐሳብ የተሠሩ የማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ማግኘት አልቻሉም። በየከተሞች ሜዳዎች ቢኖሩም በወጉ የተሠሩ አይደሉም ባይ ናቸው። ስለኾነም ታዳጊዎች የሚሰለጥኑት፣ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ክፍት ቦታዎችን በመፈለግ እና መኪና መንገድ ላይ ጭምር ኾኖ አግኝተውታል።
አቶ አብርሃም ጥናታቸውን መሠረት አድርገው እንዳብራሩት የክልሉን የስፖርት እድገት ቀፍድደው ከያዙት ምክንያቶች አንዱ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች እጥረት ነው ብለዋል። ይህ ሲባል ግን ምቹ ያልኾኑ እና ግብዓት የሌላቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በሁሉም ከተሞች የሉም ለማለት አይደለም። ሜዳዎች ለስፖርቱ እንቅስቃሴ እና እድገት የሚበጁ መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉላቸው ለሥራ ያልተመቹ ናቸው ለማለት እንጅ።
አቶ አብርሃም አክለውም ከጥናታቸው እንደተረዱት በክልሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የነበሩ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለሌላ ተግባር ሲውሉ ሀይ ባይ መጥፋቱ ሌላኛው ተግዳሮት ኾኖ አግኝተውታል፡፡ ይህ ደግሞ ጉዳዩን”በእንቅርት ላይ ጀሮ ገድፍ “አድርጎታል ብለዋል።
ምሁሩ ጉዳዩን ከጎረቤት ሀገራት ጋር አነጻጽረውታልም። በደቡብ ሱዳን ከባሕር ዳር ጋር አቻ በሚኾን ከተማ 18 ዘመናዊ የቅርጫት ኳስ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች አሉት ነው ያሉት። በእነዚህ ሥፍራዎች በርካታ ታዳጊዎች ይሰለጥናሉ። በስልጠናው ልቀው የሚወጡት ደግሞ በቡድን እንዲታቀፉ ይደረጋሉ። በአማካይ ደቡብ ሱዳን በየዓመቱ ከ10 በላይ የመረብ ኳስ ተጫዋቾችን ወደ ቻይና ክለቦች ትልካለች ነው ያሉት። ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾችንም ወደ እስያ ሀገራት ቡድኖች ይልካሉ ብለዋል።
በኬንያም በሞምባሳ ከተማ ብቻ 20 የእግር ኳስ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ሲኖሩ በአማራ ክልል ከተሞች ለእግር ኳስ፣ መረብ ኳስ እና ቅርጫት ኳስ ግብዓት የተሟላላቸው፣ ተገቢው ቁጥጥር እና ክትትል የሚደረግላቸው የማዘውተሪያ ሜዳዎች የሉም ሲሉ አንስተዋል። ከዚህ አንጻር በክልሉ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ባለመኖራቸው ለስፖርት የበቁ ወጣቶችን ማፍራት አልተቻለም ነው ያሉት ምሁሩ።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ሜዳ ዝግጅት ባለሙያው አቶ መልሰው ወርቁ እንዳሉት ደግሞ በከተማዋ ሰባት ካርታ ያላቸው የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ብቻ ናቸው ያሉት። ይህ ከከተማው ስፋት አንጻር በቂ አይደለም። ስለዚህ የግለሰቦች ጥያቄ ተገቢ ነው ብለዋል።
ለመፍትሔው ደግሞ ታጥረው የተቀመጡትን ቦታዎች ማጠናቀቅ ግድ እንደኾነም ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ሃብት እየተፈላለገ ነው። እስካሁን ግን ለዚህ ተብሎ የተያዘ በጀት እንደሌለ ባለሙያው አልሸሸጉም፤ ይሁን እና ያለንበትን ወቅት ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ተገቢ እንደኾነም ነው ባለሙያው የገለጹት።
ባለሙያው አክለውም አዳዲስ የመዝናኛ እና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ተገንብተው በመጠናቀቅ ላይ ስለኾኑም ከርክክብ በኋላ ችግሩ በመጠኑ ይቀንሳል ብለዋል። ቀደም ሲል “አሮጌው ዲፖ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ እየተሠራ ያለውን የጨዋታ ሜዳ በመጠቆም። በቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ “ዲያስፖራ መንደር” አካባቢም እየተገነባ ያለን ሁለገብ የመጫዎቻ ሜዳንም እንዲሁ አንስተዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ የማዘውተሪያ ሥፍራ የለም በሚለው ሐሳብ አይስማሙም። “በክልሉ ከ4 ሺህ በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አሉን “ባይ ናቸው። ከዚህ ውስጥም ከ56 በመቶ በላይ የሚኾኑት ካርታ አላቸው ፡፡ ይህ ማለት ሜዳዎች መንግሥታዊ (ሕዝባዊ) ናቸው።
አቶ እርዚቅ አክለውም በርካታ የስፖርት ማዝወተሪያ ሥፍራዎች ቢኖሩም በአግባቡ ባለመልማታቸው ተገቢውን ግልጋሎት እየሰጡ አይደለም። ስለኾነም ማኅበረሰቡን በማስተባበር የማልማት ሥራ ይጠይቀናል፤ ሰላም ባለባቸው እንደ ባሕር ዳር ባሉ ከተሞች ግን የማልማት ሥራ እየተተገበረ ነው ብለዋል። ክልሉ የገጠመው የሰላም እጦት በርካታ ሥራዎችን እንዳስተጓጓለም በመጠቆም ጭምር።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!