እንግሊዝን በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ የሚወክለው የመጨረሻ ሥብስብ ይፋ ኾኗል።

0
240

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌት ለአውሮፓ ዋንጫው የመጨረሻ ሥብስባቸውን ይፋ አድርገዋል። አሠልጣኙ ለ33 ተጫዋቾች የመጀመሪያ ጥሪ ካደረጉ በኋላ ዛሬ ሰባቱን ቀንሰው ወደ ጀርመን የሚጓዘውን ሥብስብ አሳውቀዋል።

በዚህ መሠረት ሀሪ ማጉየር፣ ጃክ ግሪሊሽ፣ ጀምስ ማዲሰን፣ ኮርተስ ጆንስ፣ ጀምስ ትራፎርድ፣ ጃርል ኮንሻህ እና ጃርድ ብራንዝ ዌት የተቀነሱ ተጫዋቾች ኾነዋል። እንደ ቢቢሲ ስፓርት መረጃ ኮቢ ማይኑ፣ ኮል ፓልመር እና አንቶኑዮ ጎርደን የመሳሰሉ ታዳጊዎች ደግሞ በአጭር ጊዜ ዋናውን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ሰብረው በመግባት በአውሮፓ ዋንጫው ሥብስብ ለመግባት ችለዋል።

ዲን ሄንደርሰን፣ አሮን ራምስዴል እና ጆርዳን ፒክፎርድ ጀርመን ላይ እንግሊዝን እንዲወክሉ የተመረጡ ግብ ጠባቂዎች ናቸው። ሊዊስ ደንክ፣ ጆ ጎሜስ፣ ማርክ ጉሂ፣ ካይል ዎከር፣ ኬረን ትሪፔር፣ ኢዝሪ ኮንሳ፣ ሉክ ሻው እና ጆን ስቶንስ የተከላካይ ቦታ ተመራጮች ናቸው። ትረንት አሌክሳንደር አርኖልድ፣ ኮነር ጋላገር፣ ኮቢ ማይኑ፣ ደክላን ራይስ እና አዳም ሀርቶን በአሠልጣኙ እምነት ያገኙ የመሀል ተጫዋቾች ሆነዋል።

አጥቂዎቹ ደግሞ ጁዲ ቤሊንግሀም፣ ሀሪ ኬን፣ ኦሌ ዋትኪንስ፣ ጃሮድ በዊን፣ ኢብሪቺ እዜ፣ ፊል ፎደን፣ አንቶኑዮ ጎርደን፣ ቡካዮ ሳካ፣ ኮል ፓልመር እና አይቫን ቶኒ ኾነዋል።

ዘጋቢ:-አስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here