“ኢትዮጵያ የጊኒ ቢሳው ብሔራዊ ቡድንን የማሸነፍ ዕድሏ ሰፊ ነው” ተባለ።

0
283

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ነገ ኢትዮጵያ እና ጊኒ ቢሳው በስታዲዮ ናሲዮናል 24 ደሴተምብሮ ስታዲየም ይጫወታሉ፡፡ በምድብ አንድ የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ሁለት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ይኽውም ሞሮኮ ላይ ከሴራሊዮን ጋር ባደረገው ጨዋታ ዜሮ ለዜሮ ተለያይቶ በቡርኪና ፋሶ 3 ለ 0 መሸነፉ አይዘነጋም፡፡ በዚኽም መሠረት ዋሊያዎቹ በአንድ ነጥብ እና በሦስት የግብ ዕዳ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከወራት ረፍት በኋላም ብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ቢሳው እና ጅቡቲ ጋር ለሚያደርጋቸው የምድብ ጨዋታዎች አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ሁነኛ ያሏቸውን ተጫዋቾች በመምረጥ ልምምድ መሥራታቸው ይታወሳል፡፡ ቡድኑ ነገ ላለበት ጨዋታም ወደ ጊኒቢሳው ከተማ ከገባ በኋላ በሊኖ ኮሬያ ስታዲየም ላይ ልምምድ መሥራቱም ተዘግቧል፡፡

አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ወጣት ተጫዋቾችን በማሠባሠባቸው ጨዋታው አይከብዳቸውም መባሉን የዘገበው ኢኤስፒኤን ነው፡፡ እንደዘገባው በተለይ የጊኒ ቢሳው ቡድን ከ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መልስ መጋቢት 2016 ዓ.ም ሱዳንን በወዳጅነት ጨዋታ ብታሸንፍም የተከላካይ ክፍላቸው ደካማ ነበር፤ የብረት አጥር ነው የሚባለው ተከላካዩ ሜንዴስም በቅጣት ምክንያት የነገው ጨዋታ ያልፈዋል ነው የተባለው፡፡

ጊኒ ቢሳው ባለፉት አራት ጨዋታዎች በአማካይ 0 ነጥብ 5 ግብ አስቆጥራለች፤ ይህ ደግሞ አጥቂዎቹ ማውሮ ሮድሪገስ፣ ባልዴ እና ፍራንኩሊኖ እምብዛም በጥሩ ብቃት ላይ አለመገኘታቸውን ያሳያል እየተባለ ነው። አማካይ ስፍራ ተጫዋቾቹ ጃኒዮ ቢክል እና ዳልሲዮ በልምምድ ወቅት መደባደባቸውም ተዘግቧል፡፡

ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂዎች መልካም አጋጣሚ ይኾንላቸዋል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚ ጊኒ ቢሳው በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ ምክንያት አሠልጣኝ ከባሲሮ ካንዴን በማሰናበት የቀድሞ የፉልሃም አሠልጣኝ ሉዊስ ቦአ ሞርቴን ተተኪ አድርገው ሾመዋል።

የቡድኑ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ አጀማመራቸው ጥሩ የሚባል ቢኾንም የመልበሻ ክፍላቸው ሁሌም በንትርክ መታመሱ ተነግሯል፡፡ ይህም ኾኖ ብሔራዊ ቡድኑ በሕዳር 2016 ዓ.ም ከጅቡቲ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 1 ለ 0 አሸንፏል። የማሸነፊያ ግቧንም በሲዊዝ ሱፐር ሊግ የሚጫወተው ሰባት ቁጥሩ ማዑሩ ሮደሪገስ ማስቆጠሩ አይዘነጋም፡፡

የጊኒ ቢሳው ብሔራዊ ቡድን ከቡርኪና ፋሶ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ደግሞ በአንድ አቻ ውጤት ነው ያጠናቀቀው፤ አንዷን ግብም በፈረንሳዩ ሊዮን ቡድን የሚጫወተው ማማ ሳምባ ባላዴ ማስቆጠሩ ይታዎሳል፡፡ ተጫዋቹ የቡድኑ ሞተር ነው ቢባልም መጠነኛ ጉዳት እንዳጋጠመው ተጠቁሟል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ እና አንድ ንጹህ ግብ በመያዝ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ እና ጊኒ ቢሳው የሚገኙበትን ምድብ አንድ ግብጽ በስድስት ነጥብ ትመራዋለች፡፡ ቡርኪና ፋሶ በአራት ነጥብ ሁለተኛ፣ አራት ነጥብ ያላት እና በግብ ክፍያ የተበለጠችው ጊኒ ቢሳው ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ ሴራሊዮን በአንድ ነጥብ አራተኛ እና በግብ ክፍያ የተቀለጠችው ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ አምስተኛ ላይ ትገኛለች። ጅቡቲ ያለምንም ነጥብ የመጨረሻው ስድስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here