ዘረኝነት ያጎደፈው ነጭ ማልያ!

0
214

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

ጀርመን በእግር ኳስ ስኬት ከሚቀናባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ሀገሪቱ አራት ጊዜ የትልቁ የእግር ኳስ ውድድር የዓለም ዋንጫ ባለቤት ናት። በአውሮፓ ዋንጫ ደግሞ ሦስት ዋንጫዎችን ማሳካት የቻለ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን አላት በታሪክ። በክለብ ደረጃም ባየርሙኒክን የመሰለ ዝናው በዓልም የናኘ፣ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ስደስት ጊዜ ዋንጫውን ያነሳ ክለብ ባለቤት ናት።

እንዲህ በእግር ኳስ ጥሩ ስም ያላት ሀገር ከሰሞኑ ጥላዋን የሚገፍ ነገር ገጥሟታል። አርዲ የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከሰሞኑ አደረኩት ያለውን ጥናት ይፋ ሲያደረግ በርካታ ጀርመናውያን ጥቁር ተጫዋቾች የጀርመንን መለያ እንዲለብሱ አይፈልጉም ብሏል። በደይሊሜል መረጃ መሰረት ጥናቱ 1ሺህ 304 ጀርመናውያንን አሳትፏል። ጥያቄው ጀርመንን የሚወክሉ ተጫዋቾችን የቆዳ ቀለም እና የዘር ግንድ የተመለከተም ነው።

በጥናቱ ውጤት መሠረት ከተጠየቁት ጀርመናዊያን መካከል 21 በመቶዎቹ ነጩን የጀርመን መለያ ነጭ ተጫዋቾች እንዲለብሱት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ይህ ማለት ሀገራችን በጥቁር ተጫዋቾች ተወክላ ማየት አንፈልግም ማለታቸው ነው። ከጠየቁት 17 በመቶዎቹ ደግሞ በአሁኑ ብሔራዊ ቡድናቸው ውስጥ ኢልካይ ጉንዱጋን አምበል መኾኑ አሳፋሪ ነው ሲሉ ገልጸውታል። ምክንያታቸው ደግሞ ተጫዋቹ በደም ቱርካዊ እንጅ ጀርመናዊ አይደለም የሚል ነው።

የጥናቱን ይፋ መኾን ተከትሎ በጀርመን ዜጎች እንዲሁም ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች መካከል ያለው ስንጥቅ ይበልጥ እንዳይሰፋ ተሰግቷል። ለዚህም ይመስላል ጥናቱን የሚኮንኑ ሀሳቦች በስፋት እየወጡ ያሉት። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ጆሽዋ ኪሚች ጥናቱ በራሱ ፍጹም ዘረኝነት ነው ብሏል። እግር ኳስ የተለያየ የቆዳ ቀለም እና ሃይማኖት ያላቸውን አንድ ያደርጋል፤ እውነታው ይሄ ኾኖ ሳለ በተቃራኒው የሚነሳ ሀሳብ ስሜት የለውም የሚል ሀሳብ ሰጥቷል። ከተለያየ የቆዳ ቀለም እና ሃይማኖት ባይመጡ ኖሮ ብዙ ተጫዋቾችን እናጣ ነበር ሲልም አክሏል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ጁሊያን ናግሊስማንም ጥናቱን ኮንነዋል። እንዲህ አይነት ጥያቄ መጠየቁ እብደት ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። የተለያየ ባሕል፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ያላቸው በአንድ መሠባሠባቸው ለተሻለ ስኬት እንደሚያበቃ እግር ኳስ አረዓያ መኾን አለበት ማለታቸውን ፉትቦል አፕ የተሰኘ የመረጃ ምንጭ ጽፏል። ጀርመን በቆዳ ቀለም ወይም ሃይማኖት ሳይኾን ችሎታ ባላቸው ተጫዋቾች እንደምትወከልም አረጋግጠዋል።

“በአውሮፓ ዋንጫ ሜዳ ላይ በልጠው የታዩ ጀርመናውያን ሁሉ ነጬን የጀርመን ማሊያ ይለብሳሉ። ለተሻለ ስኬትም ያላቸውን ሁሉ ይሰጣሉ፤ አየሠራን ያለነውም ይሄን ለማደረግ ነው” ብለዋል። “ተስፋ አደርጋለሁ እንዲህ ያለ የማይረባ ጥናት ሁለተኛ እንደማላነብ” በማለትም የጥናቱን መደረግ አብዝተው ተችተዋል።

ጥናቱን በማድረጋቸው ብዙ እየተተቹ የሚገኙት የኤርዲ ጣቢያ አዘጋጆች ይሄ የእግር ኳሱ ዘረኝነት የማኅበረሰቡን አውነታ የሚያሳይ ነው፤ ጀርመን የደበቀችው ጉዷን በአደባባይ አሳየን እንጅ ምን አጠፋን ሲሉ መልሰዋል። በጥናቱ ሀሳብ እንዲሰጡ የተደረጉ እና ጀርመናዊ ሳይኾኑ ለጀርመን ተጫውተው ያለፉ ግለሰቦችም ዘረኝነት በጀርመን እግር ኳስ አንገታችን አስደፍቶን ኑሯል ሲሉ መስክረዋል። ትውልዱ ጋና የኾነው ጊራልድ አሳማዋህ በተጫዋቾች ሳይቀር የዘረኝነት ጥቃት ማስተናገዱን ያስታውሳል።ኒግሮ /ጥቁር/ መባል የተለመደ ነበር ብሏል።

የቀድሞው የአርሰናል ተከላካይ ሽኮርዳን ሙስጣፊ የዘር ግንዱ ከአልባኒያ እና ሜቄዶንያ ነው። ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን የመጫወት እድልም ነበረው። ጀርመናዊያን የእግር ኳስ ችሎታህን ሳይኾን የሀገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር መዘመር አለመዘመርን መስፈርት ያደርጋሉ ሲል ደጋፊዎች ዘረኛ መኾናቸውን ጠቅሷል።
ሊጀመር ቀናት በቀረው የአውሮፓ ዋንጫ የጀርመን ቡድን ሥብሥብ ውስጥ በርካታ ጥቁር እና የቱርክ የዘር ሀረግ ያላቸው ተጫዋቾች ይገኛሉ። አንቶኒ ሩገር፣ ሊሮይ ሳኔ፣ ጀማል ሙሴላ፣ ኢልካይ ጉንዱጋን ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑን በቋሚነት የሚያገለግሉ ወሳኝ ተጫዋቾች ናቸው። በዘረኞቹ ደጋፊዎች ግን የጀርመንን ነጭ መለያ ለመልበስ አጥንተ ሰባራ ተብለዋል።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የ2014ን የዓለም ዋንጫ ሲያነሳ በርካታ በዘር ጀርመናዊ ያልኾኑ ተጫዋቾች ነበሩ። ለብሔራዊ ቡድኑ ስኬትም የቆዳ፣ የሃይማኖት እና ዜግነት ልዩነት ያልፈተነው አንድነት በብዙ ተሞግሷል። ከዓለም ዋንጫ ማግስት ብሔራዊ ቡድኑ ደክሞ ሲገኝ ግን አካላቸው እንጅ ልባቸው ጀርመናዊ ያልኾኑ ተጫዋቾች በሚል አጥንት ተቆጥሮ እነ ሚሶት ኦዝል መከራቸውን በሉ።

የያኔው የአርሰናል ተጫዋች ኦዝልም ስናሸንፍ ጀርመናዊ ስንሸነፍ ደግሞ ስደተኛ እንባላለን ሲል የጀርመናዊያንን ዘረኝነት መስክሮ ጀርመንን መወከል በቃኝ ብሏል። ጀርመናዊያን በታሪክ በናዚ ዘመን ራሳቸውን ከሰው በላይ ብለው ታሪክ ይቅር የማይለው ጭካኔ በሰው ልጅ ፈጽመዋል። በተለይ በሚሊዮን አይሁዳዊያን ላይ የፈጸሙት ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥን ተግባር አሁንም ድረስ ያስወቅሳቸዋል። በዚህ ከማፈር እና ከመማር ይልቅ አሁንም በሀገሪቱ የናዚን አሳፋሪ ተግባር እንደ ጀብድ የሚቆጥሩ ፣ ራሳቸውን በዘረኝነት ያረከሱ ጀርመናውያን ጥቂት አይደሉም። ጀርመን ለተመረጡት ጀርመናውያን ብቻ ናት የሚል ሀሳብንም ያራምዳሉ። የእነዚህ ሰዎች ሀሳብ በማኅበረሰቡም በእግር ኳሱም ውስጥ ይታያል።

ይሄ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ብዝኀነት በተለወጠችው ጀርመን ቁጣን እና መከፋፈልን እየፈጠረ ነው። ከሰሞኑ ይፋ የኾነው ጥናት ውጤትም የተፈራው በልዩነቶች ለተዋቀረው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ውጤት ማጣት ምክንያት እንዳይኾን ነው። ጀርመን ራሷ በምታስተናግደው እና ከቀናት በኋላ በሚጀምረው የአውሮፓ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከስኮትላንድ ጋር ታደርጋለች።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here