ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብቻ ሕልም አልም፣ ሕልምህን እውን ለማድረግ ጠንክረህ ሥራ፣ ለዓላማህ በርታ እንጂ አንድ ቀን ሕልምህ እውን መኾኑ አይቀርም፡፡ ሕልም ማለም ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ ሕልም በጠንካራ ሥራ ሲታገዝ እውን ይኾናል፡፡ ገና በለጋ እድሜው ነጩን መለያ አሻግሮ ተመለከተ፡፡ በነጩ መለያ የደመቁ ከዋክብት ቀልቡን ገዙት፡፡ እነርሱ የለበሱትን መለያ ለብሶ በዓለም እግር ኳስ ይደምቅ ዘንድ ወደደ፡፡ ፓሪስ ተቀምጦ ሕልሙን በማድሪድ ላይ ጣለ፡፡ ማድሪድ የሕልሙ ከተማ ኾነች፡፡ ሪያል ማድሪድ ደግሞ የሕልሙ ክለብ፡፡
በትውልድ መንደሩ ከአብሮ አደጎቹ ጋር ኳስ ሲጫዎት አንድ ቀን በማድሪድ መለያ እንደሚጫወት በልቡ ያሰብ ነበር፡፡ የእግር ኳስ ሕይዎቱ በመንደር ተጀመሮ በመንደር የሚጠናቀቅ ሳይኾን በዓለም ቁንጮ ደርሶ እንደሚጠናቀቅ ለልቡ ደጋግሞ ይነግረዋል፡፡ ማደሪያ ክፍሉ በማድሪድ ከዋክብት ፎቶዎች ተመልተዋል፡፡ በተለይም በክርስቲያኖ ሮናልዶ ፎቶ፡፡ የዓለም ሚደያዎች የንግግራቸው መክፈቻ የሚያደርጉት፣ የንግግራቸውም መዚያጊያ የሚያደርጉት፣ ከሊዝበን፣ ማንችሰተር፣ ከማንችስተር ማድሪድ እያለ የደመቀው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የእርሱ አርዓያ ነው፡፡
በክርስቲያኖ ሮናልዶ ፎቶዎች ባሸበረቀች ክፍሉ ሲተኛም፣ ሲነሳም አንድ ቀን እርሱ በደመቀበት ሜዳ ላይ እንደሚደምቅ ያስብ ነበር ኪሊያን ምባፔ፡፡ የተወለደው በፈንሳይዋ ዋና ከተማ ፓሪስ ነው፡፡ ያደገው ሴን ሴንት ዴንስ ነው፡፡ አባቱ ዊልፍሬድ ምባፔ ይሰኛሉ፡፡ የዘር ሀረጋቸው የሚመዘዘው ከአፍሪካዊቷ ሀገር ካሜሮን ነው፡፡ ወደ ፓሪስ ያቀኑት የተሻለ ሕይዎትን ለመምራት ነው፡፡ እናቱ ደግሞ ፋይዛ ላማሪ ይባላሉ፡፡ የእርሳቸው የዘር ሀገር የሚመዘዘው ከአፍሪካዊቷ ሀገር አልጀሪያ ነው፡፡ እናት እና አባቱ ልጃቸው ፍላጎቱን እንዲከተል አበረታቱት፡፡ ሂድ ግፋበት፣ ጠንክር፣ ከጎንህ ነን አሉት፡፡
እንኳን በርታ አይዞህ የሚለው ሰው አግኝቶ እርሱም ሕልሙ በእግር ኳስ መድመቅ ነውና ሕልሙን ገፋበት፡፡ በአባቱ አሰልጣኝነት በቦንዲ እግር ኳስን በብርታት ጀመረ፡፡ ለእግር ኳስ የተሰጠ እና የእግር ኳስ እድገቱ የሚደንቅ ነበርና ብዙም ሳይቆይ ወደ ሞናኮ የታዳጊዎች አካዳሚ ተቀላቀለ፡፡ ወደ ሞናኮ የታዳጊዎች አካዳሚ ሲቀላቀል ከቤት መውጣት ነበረበት፡፡ ከሀገሩ ግን አልወጣም፡፡
ለዚያ ሕልመኛ ታዳጊ ከቤት መውጣት ከባድ ቢሆንም ሕልሙን ለመኖር የሚከፈል መስዋት ነውና ከቤቱ ርቆ ሄደ፡፡ ምባፔ የታዳጊዎችን አካዳሚ እንደተቀላቀለ ጨዋታዎችን ማድረግ ጀመረ፡፡ ይህ ባለተሰጥኦ ታዳጊ በሞናኮ ቤት አስደናቂ የእግር ኳስ ጥበብን ማሳየት ጀመረ፡፡ የሞናኮ አሰልጣኞችን፣ ታደጊዎችን እና ጨዋታ ለመመልከት የሚገቡ ደጋፊዎችን ቀለብ ሳበ፡፡ ከአንደኛው ሜዳ ወደ ሌላኛው ሜዳ ኳስ እየገፋ የተቃራኒ ተጫዋቾችን እያታለለ ሲያልፍ ከፍጥነቱ አይቀንስም፣ በተቃራኒ ተጨዋቾች ለመያዝ በሚያስቸግር ፍጥነት እና የኳስ ቁጥጥር ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ይገሰግሳል፡፡ በአስደናቂ ፍጥነት እና የኳስ አገፋፍ ሄዶ አስደናቂ ግብ ያስቆጥራል፤ ከላበዘሊያም ኳሱን አመቻችቶ ያቀብላል፡፡
ዋን ፉትቦል በዘገበው የኪሊያን ሜባፔ እድገት የሚደንቅ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ በዓለም አቀፍ መድረክ የራሱን አሻራ አኑሯል ይላል፡፡ ሜባፔ ከሞናኮ ጋር ሲጫወት የዓለምን ቀልብ ሳበ፡፡ ሞናኮ የፈረንሳይ ሊግ ዋንጫን እንዲያነሳ አደረገ፡፡ በቀይ እና ነጩ የሞናኮ መለያ አሸብርቆ ከመስመር ኳስ ይዞ በፍጥነት ወደ ተቃራኑ የግብ ክልል የሚገሰግሰው ሕልመኛ የታላላቅ አሰልጣኞችንና የክለቦችን ቀለብ ሳበ፡፡ ከሞናኮ ከፍ ባለ ቡድን መጫወት እንዳለበት ተነገረ፡፡ ያ በታደጊ እድሜው በክርስቲያኖ ሮናልዶ መለያ በደመቀች ማደሪያው ሆኖ ትልቅነትን ሲያልም የነበረውን ሕልመኛ በጠንካራ ስራው ታግዞ ወደ ሕልሙ መቅረብ ጀመረ፡፡
በወቅቱ የዓለም ከዋክብትን እያሳደደ የነበረው የትውልድ ከተማው ክለብ ፓሪስ ሴንት ጀርመን የእርሱን ፊርማ ለማግኘት ቋመጠ፡፡ ዋን ፉትቦል የፈረንሳዩዋ ዋና ከተማ ፓሪስ ልጇን በጉጉት እየጠበቀች ነበር፡፡ ሜባፔም ለፒኤስጂ ሲፈርም ሕልሟ እውን ኾነ ይላል፡፡ ኮከቡ ብዙም ሳይቆይ የሰባት ቁጥር መለያን ተሰጠው፡፡ ሰባት ቁጥር መለያን አጥልቆ በፓርክ ደንስ ፍራንስ ስታዲዬም ዓለምን በሚያስደንቅ ጥበብ ይጎመራ ጀመር፡፡ በፒኤሲጂ መለያ አስደናቂ ግቦችን አስቆጠረ፡፡ ለቡድን አጋሮቹም ያለቁ ኳሶችን ለጎል አመቻችቶ አቀበለ፡፡ በዓለም እግር ኳስም የራሱን አሻራ አስቀመጠ፡፡ በክለብ ብቻ ሳይሆን ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ጋርም አሻራውን አሳረፈ፡፡
ይህ ታደጊ በ2018 የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ግብ በማስቆጠር ከብራዚላዊው ፔሌ በመቀጠል በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ተባለ፡፡ በተሳተፈባቸው ሁለት የዓለም ዋንጫዎች በሁለቱም ለፍጻሜ ደረሰ፡፡ የመጀመሪያውን የፍጻሜ ጨዋታ ድል አድርጎ የዓለም ዋንጫውን ወደ ሀገሩ ፈረንሳይ ወሰደ፡፡ አስቀድማ ገና ስትናፍቀው የነበረችው የትውልድ ከተማው ፓሪስ የዓለም ዋንጫን ይዞላት የመጣውን ልጇን አክብራ ተቀበለችው፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቅንጡ ቤተ መንግሥታቸው ለሜባፔና ለጓደኞቹ ደማቅ አቀባበል አደረጉ፡፡ ሁለተኛውን የዓለም ዋንጫ ግን በመለያ ምት ሀገሩ ተሸንፋ ዋንጫውን አጣ፡፡ ነገር ግን በፍጻሜው ጨዋታ እንደ እርሱ የጎላ ተጨዋች አልነበረም፡፡ በፍጻሜው ጨዋታ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰራ፡፡ በውድድሩም ኮከብ ግብ አግቢ ኾኖ የወርቅ ጫማውን ይዞ ወደ ፈረንሳይ ተመለሰ፡፡ በ2022 የኳታሪ የዓለም ዋንጫ በፍጻሜው ሀገሩ ስትሸነፍ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ “ጠንክረን እንመለሳለን” ሲል ጻፈ፡፡ ይህም የልጁን ጠንክሮ መስራት እና ለድል መትጋትን የሚያሳይ ነበር፡፡
ዋን ፉትቦል የእርሱ የእግር ኳስ ሕይወት በእናት ሀገሩ ላይ አምሯል፡፡ ነገር ግን ሪያል ማድሪድን በልቡ ይዞ ይኖር ነበር ይላል፡፡ አንድ ቀን በነጩ መለያ ደምቆ በሳንቲያጎ ቤርናቦው መጫወት የእርሱ የሁልጊዜም ሕልም ነውና፡፡ የፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ ፒኤስጂ በክለቡ ይቆይ ዘንድ ብዙ ጥረት አደረገ፡፡ ሜባፔ ግን ሕልሙን ይኖር ዘንድ ወደደ፡፡ የክለቡ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ከሆነበት ፔኤስጂ ወጥቶ ወደ ማድሪድ ለመሄድ ወሰነ፡፡ የፔኤሲጄው አለቃ ናስር ቢን ጋህነም አል ካሊፋ ሜባፔን ለማቆየት ብዙ ጥረት አደረጉ ሜባፔ ግን ተውኝ ሕልሜን ልኑርበት አለ፡፡
አሁን ኪሊያን ሜባፔ ሕልሙን እውን ለማድረግ ወደ ማድሪድ መሄዱን አረጋግጧል፡፡ ይህ ዝውውር እንደ ልብ አንጠልጣይ ተከታታይ ድራማ ወይም እንደ ትራጄዲ ተውኔት በዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት ሲጠብቅ ኖሯል፤ በመጨረሻም በጥሩ አፈጻጸም ተጠናቅቋል፡፡ ሜባፔ ወደ ማድሪድ መሄዱ ከተረጋገጠ በኋላ “ሕልሜ እውን ኾኗል” ብሏል፡፡ ሜባፔ በነጩ መለያ ደምቆ በሳንቲያጎ ቤርናቦው የሚያቆየውን የአምስት ዓመታት ውል ተፈራርሟል፡፡
ሕልመኛው ኮኮብ በነጩ ቤት በዓመት 15 ሚሊዮን ዩሮ ይከፈለዋል፡፡ 150 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ የፊርማ ቦነስ በአምስት ዓመታት ውስጥ እንደሚከፈለው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ሜባፔ ሕልሙ እውን የሆነበትን ዝውውር ከፈጸመ በኋላ “አሁን ምን ያህል እንደተደሰትኩ ማንም ሊረዳኝ አይችልም” ሲል የደስታው ወሰን ጥግ መድረሱን በኢንስታግራም ገጹ ጽፏል፡፡ ሜባፔ ህልሜ እውን ሆነ። ወደ ህልሜ ክለብ በመቀላቀሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ኩራትም ይሰማኛል ይላል፡፡
ወደ ስፔኗ ዋና ከተማ ከብራዚላውያኑ አጥቂዎች ቪኒስስ ጁኒየር ፣ ሮድሪጎ፤ ከአዲሱ ፈራሚ ኤንድሪክ ፤ እንግሊዛዊው አማካኝ ጁድ ቤሊንግሃም ጋር ይጫወታል፡፡ ይሄም አሰላለፍ አዲሱን የጋላክቲኮ ዘመን እንደሚያመጣ ይጠበቃል ይላል ቢቢሲ በዘገባው፡፡ በ2017 ከሞናኮ በውሰት ፔኤስጂን የተቀላቀለው ሜባፔ 256 ጎሎችን በማስቆጠር የክለቡ የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡ ሜባፔ ባለፉት ስድስት ዓመታት በፈረንሳይ ሊግ አንድ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመኾን አጠናቅቋል፡፡ ሜባፒ ሰባት የፈረንሳይ ሊግ አንድ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡ አንድ ከሞናኮ ጋር ሲያሸንፍ ስድስቱን ደግሞ ከፒኤስጂ ጋር ነው ያሸነፈው፡፡ ሜባፔ የሀገሩ ፈረንሳይ ቁንጮው ተጨዋች ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ቡድኑም አምበል ነው፡፡ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጨምሮ ፈረንሳውያን የሚሳሱለት፣ የሚመኩበት እና የሚኮሩበት ኮከብ ነው፡፡
ኪሊያን ሜባፔ አሁን በዚያች ማደሪያ ጎጆው ኾኖ ሲያልመው በነበረው ክለብ ደርሷል፡፡ አሁን በአሻገር ሳይሆን በሳንቲያጎ ቤርናቦው ነጩን መለያ አጥልቆ ይጫወታል፡፡ ሕልሙን በእውን ይኖራል፡፡ ታላቅ ሕልም ማለም፣ ጠንክሮ መሥራት ሕልምን እውን ያደርጋልና፡፡ ታላቅ ሕልም አልሙ፣ ታላቅ ሥራም ሥሩ በመጨረሻም ሁሉም ይሳካል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአርያነት የሚጠቀሱ የዓለም ከዋክብት መልተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ፈረንሳዊው ኮኮብ ሜባፔ አንዱ ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!