ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብራዚላዊው የሪያል ማድሪድ የፊት መስመር ተጫዋች ቪኒሰስ ጁኒየር የአውሮፓ ቻምዮንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ኾኖ ተመርጧል፡፡ በኃያሉ ክለብ ሪያል ማድሪድ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የአውሮፓ ቻምዮንስ ሊግ የዓመቱን ምርጥ ተጫዋቾች ይፋ አድርጓል፡፡ የሪያል ማድሪዱ ቪኒሰስ ጁኒየር የውድድሩ ዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ሲሸለም ሌላኛው የክለቡ አጋሩ እንግሊዛዊ ጁድ ቤሊንግሃም የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ተብሏል፡፡
የቻምፒዮንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ቡድን ሥብሥብም ይፋ ኾኗል፡፡ ለፍጻሜ የደረሱት ቦርሲያ ዶርትመንድ እና ሪያል ማድሪድ እያንዳንዳቸው አራት አራት ተጫዋቾችን አስመርጠዋል፡፡ በግብ ጠባቂነት የዶርትመንዱ ግብ ጠባቂ ኮብል ሲመረጥ፣ በተከላካይ መስመር የሪያል ማድሪዶቹ ዳኒ ካርቫሃል፣ አንቶኒ ሮድሪገር፣ የቦርሲያ ዶትርመንዶቹ ማት ሐመልስ እና ኢያን ኢትሃን ማትሰ ተመርጠዋል፡፡
በአማካኝ ስፍራ የፓሪስ ሴንት ጀርሜኑ ቪቲኒሃ፣ የሪያል ማድሪዱ ጁድ ቢሊንግሃም፣ የቦርሲያ ዶትርመንዱ ማርሴል ሳቢስተዘር ተመርጠዋል፡፡ በአጥቂ ስፍራ ደግሞ የሪያል ማድሪዱ ቪኒሰስ ጁኒየር፣ የባየርን ሙኒኩ ሀሪ ኬን እና የማንችሰተር ሲቲው ፊል ፎደን ተመርጠዋል፡፡ የ2023/24 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ከቀናት በፊት በሪያል ማድሪድ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ሪያል ማድሪድ ዋንጫውን ማሸነፉን ተከትሎ በታሪኩ ለ15ኛ ጊዜ ኾኖ ተመዝግቧል፡፡ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንዳስነበበው ይሄ ቁጥር ሪያል ማድሪድን ከየትኛውም የአውሮፓ ክለብ በላይ ያስቀምጠዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!