የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጉድለቶችን እየሞላ ነው!

0
257

ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም 42 ሄክታር መሬት ይዞታ አለው። የስታዲየሙ ግንባታ የተጀመረው በ2002 ዓ.ም በ780 ሚሊየን ብር በጀት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። አብዛኛው ሥራ በመጠናቀቁም የተለያዩ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ተስተናግደውበታል። ከዚህ ባለፈም አህጉራዊ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ተካሂደውበታል።

ይሁን እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጥቅምት7/2014 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ስታዲየሙን ተመልክቶ አህጉራዊ ጨዋታዎች እንዳይደረጉበት አግዶታል። “ይህ ግዙፍ ስታዲየም ምን ምን ጉዳዮች ስላልተሟሉለት ነው በካፍ የታገደው?” መባሉ አይቀርም። ካፍ በእግድ ደብዳቤው ላይ በዋናነት የስታዲየሙ የመጫወቻ ሳር ደረጃውን የጠበቀ አለመኾኑን አስታውቋል። ስለኾነም ሳሩ በተፈጥሮ ሳር መቀየር እንዳለበት ምክረ ሐሳብም አስቀምጧል።

አንድ ስታዲየም ለውድድር ብቁ ከሚያስብሉት ጉዳዮች አንዱ ጨዋታዎችን በምሽትም ማስተናገድ ሲችል ነው ያለው ካፍ የባሕር ዳር ስታዲየም ከዚህ አንጻር ከደረጃ በታች በመኾኑ ጨዋታዎችን ማስተናገድ አይችልም ብሏል። ደረጃቸውን ያሟሉ የመልበሻ ክፍሎች እንዲኖሩትም ካፍ ጠይቋል።

በተጨማሪም ተመልካቹ ዘና ብሎ ጨዋታዎችን የሚያይበት ምቾት ያለው ወንበር፣ እንግዶች በሚገኙበት ቦታ የዋይ ፋይ አገልግሎት፣ ቴሌቪዥን እና የድምጽ ሲስተም፣ የሚዲያ ክፍሎች፣ የመኪና ማቆሚያ፣ በምሽት ሳይቀር ልምምድ ሊያሠራ የሚችል ሜዳ እና ሌሎች ጉዳዮች አለመኖር ለባሕር ዳር ብሔራዊ ስታዲየም የመታገድ ምክንያት ናቸው ብሏል ካፍ።

የተባሉትን ጉዳዮች በጸጋ የተቀበለው የአማራ ክልል መንግሥትም 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በመመደብ የካፍን ብቻ ሳይኾን የፊፋንም ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ሊመልስ የሚችል ሥራ እያከናዎነ ነው። ካፍ ዛሬ ላይ በእጥረት ያነሳቸውን ብቻ ሳይኾን ነገ ላይ ሊጠይቅ የሚችለውን ጥያቄ ታሳቢ በማድረግ ከ50+1 በላይ ቀሪ ሥራዎችን ወደ ማጠናቅ ተደርሷል። እንደ ክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እርዚቅ ኢሳ ሀሳብ።

ኃላፊው ለአሚኮ እንደገለጹት ስታዲየሙ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንዲችል ኾኖ እየተሠራ ነው፡፡ ይህም ማለት ከዋናው የእግር ኳስ መጫወቻ በተጨማሪ በቅጥር ግቢው ሁለት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሜዳዎች ግንባታቸው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ ግንባታውን ደግሞ 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአስደማሚ ኹኔታ የተካሄደባቸውን የኮትዲቮር ስታዲየሞችን የገነባው የፈረንሳይ ኩባንያ እየገነባው መኾኑን ነው ኃላፊው የጠቆሙት።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የስታዲየሙ ቅጥር ግቢ የአጥር ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል። ወደ ስታዲየሙ የሚያስገቡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ሁለት በሮች ወደ አምስት እንዲያድጉ ተደርጓል። እንደ አቶ አርዚቅ ማብራሪያ 42 ሄክታሩን መሬት የማመቻቸት ሥራ መከናዎኑን ተናግረዋል። ሦስቱን የመጫዎቻ ሜዳዎች አፈር የማልበስ ሥራም መገባደዱን ተናግረዋል። አራት ቡድኖች በአንድ ጊዜ ትጥቅ ሊቀይሩባቸው የሚችሉ የሴት እና ወንድ ተጫዋቾች፣ የዳኞች፣ የኳስ አቀባዮች ክፍሎች ተስርተው ተጠናቀዋል።

አቶ እርዚቅ ጨምረው እንደገለጹት ስታዲየሙ ጨዋታ ሲኖር ብቻ የሚከፈት ሳይኾን በሌሎች ቀናትም ሻይ እና ቡና የሚሸጡባቸው ዘመናዊ ካፍቴሪያዎች እና ጅም ቤቶችም ይኖሩታል ብለዋል፡፡ ካፍ እና ፊፋ በጠየቁት መሠረት ስታዲየሙ በምሽትም ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ የመብራት ግዥ እንደተከናዎነ ኃላፊው ተናግረዋል።

ካፍ ስታዲየሙ ጎድሎታል ብሎ ካንሳው ጥያቄ አንዱ የሚዲያ ክፍል መኖር አለበት የሚል መኾኑን ያስታዎሱት አቶ እርዚቅ የቀጥታ ሥርጭት እና የብሎገር ክፍሎችም ከተሟላ የኢንተርኔት መሥመር ጋር እንዲኖሩት ተደርጎ በመገንባት ላይ ይገኛል። በአንድ ጊዜም 120 የመገናኛ አውታሮችን ማስተናገድ የሚችሉ ዘመናዊ ክፍሎችም ይኖሩታል። ይህም ሥራ እየተሳለጠ እንደሚገኝ አቶ እርዚቅ ተናግረዋል።

የአሳንሰር (ሊፍት) መግጠሚያ ግንባታ ተጠናቆ ሊፍት እየገባ መኾኑንም ኃላፊው ተናግረዋል። አሳንሰርን በተመለከተ ሌሎች በካፍ ይሁንታ አግኝተው የተወደሱ ስታዲየሞች የላቸውም ያሉት ኃላፊው ፊፋ ግን ሊፍት እንደሚጠይቅ አውቀን የባሕር ዳሩ ስታዲየም ሊፍት እንዲኖረው ተደርጓል ብለዋል።
በጨዋታ ወቅት ግቦችን ፣ ጨዋታዎችን እና ሌሎች ጉዳዮችን በምልሰት የሚያሳዩ እንዲሁም ሰዓት የሚጠቁሙ ግዙፍ ስክሬኖችም እየተገጠሙለት ነው ብለዋል አቶ እርዚቅ።

የስታዲየምን ደህንነት የሚጠብቁ በርካታ ካሜራዎች እና የዲጂታል ቲኬቲንግ መቆጣጠርያም ይኖረዋል ብለዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና የዓለም አቀፉን እግር ኳስ ማኀበር (ፊፋ) የደረጃ መስፈርትን ያሟላ ዘመናዊ ወንበር ለመግጠምም የወንበር ግብዓት ከውጭ ሀገር ማስገባት መጀመሩን ጠቅሰዋል።

የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የማስፋፊያ ግንባታው ሲጠናቀቅ የካፍ የመጨረሻ ምርጥ ስታድምየም የጥራት ደረጃ መመዘኛን የሚያሟላ ይኾናል ነው ያሉት። ይኸም ማለት የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ጨምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያሉ የአፍሪካ የክለብ ውድድሮችን እንዲኹም የአፍሪካ ዋንጫን የመሳሰሉ ትልልቅ ጨዋታዎችን የማስተናግድ አቅም ይኖረዋል።

በግንባታ ሂደቱ ግብዓት ከውጭ ሀገር ለማስገባት የዶላር ምንዛሬ እጥረት እንደ ነበር ያሉት አቶ እርዚቅ አሁን ግን ከፍተኛ ኃላፊዎች ባደረጉት ቁርጠኛ ርብርብ ብሔራዊ እና ንግድ ባንኮች የዶላር እጥረቱን ፈተውታል፤ በመኾኑም አስፈላጊውን ግብዓት ከውጭ ሀገር ማስገባት ተጀምሯል ነው ያሉት።

በካፍ እና በፊፋ መሥፈርት መሠረት የሜዳ ሥራው አሁን ላይ 44 በመቶ መድረሱን የገለጹት ኀላፊው የካፍ እና የፊፋ ዋነኛ ጥያቄ ኾኖ የቀረበው የመጫዎቻ ሜዳው የተፈጥሮ የሳር ዝርያ ከአውሮፖ በቅርቡ ይገባልም ብለዋል። የኤምኤች ኢንጅነሪንግ የአማካሪዎች ቡድን መሪ ኢንጅነር እስክንድር ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የግንባታ ሂደት በጥራት እና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። አሁን ባለው የግንባታ ሂደት እስከ ጥር 2017 ዓ.ም ድረስ በገባነው ውል መሠረት የካፍ ውድድሮችን ለማካሄድ ከሚያስችል በላይ አጠናቀን እናስረክባለን ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here