ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ሁለተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር ተጠናቀቀ። በኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከግንቦት 21 እስከ 24/2016ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች ውድድር ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ ውድድሩ ሁለቱንም ጾታ ያሳተፈ ሲሆን በወንዶች A ምድብ 10 ክለቦች፣ በወንዶች B ምድብ 5 ክለቦች እና በሴቶች 4 ክለቦች ተሳተፊ ሆኗል፡፡
በወንዶች A ምድብ እና በወንዶች B ምድብ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን አሸናፊ ሲሆን በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ አሽናፊ በመሆን ውድድሩን ሲያጠናቅቁ የፌዴራል ማረሚያ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ሻምፒዮና አዳዲስ ቡድኖች የተገኙበት ነው ብለዋል።
ከፍተኛ ፉክክር የታየበት መሆኑን ተናግረው በአሁኑ ሰዓት ቦክስ ከአትሌትክስ በመቀጠል የኢትዮጵያን ስም በዓለም መድረክ ከፍ እንዲል እያደረገ መኾኑን አንስተዋል። ሚኒስትሩ አክለው የቦክስ ስፖርትን የተሻለ ቦታ ለማድረስ መንግሥት የበኩለን ሚና ይጫወታል፤ በብሔራዊ ደረጃ በክለቦች መካከል ያለውን ውድድር ለማሣደግ እና ተተኪ ብሔራዊ ቦክሰኞችን ማፍራት እንዲቻል የግል ባለሀብቶች የበኩላቸውን አበርክቶ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን፣ የፌዴሬሽን ሥራ አሥፈጻሚዎችን ጨምሮ በርካታ ታዳሚያን በውድድሩ ስፍራ በመገኘት የተከታተሉ ሲሆን ለአሸናፊ ክለቦች፣ ተጨዋቾች እና አሠልጣኞች የሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!