የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ የትኛው ቡድን ይወስደው ይኾን?

0
288

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የስፔኑ ሪያል ማድሪድ እና የጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ የሻምፒዮንስ ሊግን ዋንጫ ለማንሳት ዛሬ የፍጻሜ ጨዋታ ያደርጋሉ። የ2023/24 አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት 90 ሺህ ተመልካች በሚይዘው ግዙፉ የእንግሊዝ ዌምብሌይ ስታዲየም ይደረጋል፡፡

የዌምብሌይ ስታዲየም ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታን ሲያስተናግድ የዛሬው ለስምንተኛ ጊዜ ነው። ሪያል ማድሪድ በግማሽ ፍጻሜው የጀርመኑን ባየርን ሙኒክ እንዲሁም ቦሩሲያ ዶርትሙንድ የፈረንሳዩን ፓሪስ ሴንት ዤርሜንን አሸንፈው ነው ለዋንጫ የደረሱት። ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለ17ኛ ጊዜ ለፍጻሜ ቀርቦ 14 ጊዜ ሻምፒዮን ሲኾን ሦስት ጊዜ ብቻ ዋንጫ አጥቷል።

የሪያል ማድሪድ አሠልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ እንዳሉት የዌምብሌዩ የሻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ እንዳሰጋቸው ተናግረዋል። “ሙሉ በሙሉ ‘እናሸንፋለን’ ብዬ ለመናገር ዋስትና የለኝም” ነው ያሉት አንቸሎቲ። ይሁን እና በአግባቡ አጥቅተው እና ተከላክለው በመጫዎት ስኬት ላይ ለመድረስ ማለማቸውን በመጠቆም።

የሪያል ማድሪድን ቡድን ስፔናዊው ተከላካይ ናቾ ፈርናንዴዝ በአምበልነት እንደሚመራውም አሠልጣኙ ፍንጭ ሰጥተዋል። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ የዛሬውን ጨዋታ ሳይጨምር ሁለትጊዜ ለፍጻሜ ቀርቦ እንድ ጊዜ ሻምፒዮን ኾኗል። ዶርትሙንድ (ቢጫ ለባሾቹ) ከ11 ዓመት በፊት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዌምብሌይ ስታዲየም ላይ ለፍጻሜ ደርሰው በሀገራቸው ኀያል ቡድን በባየርን ሙኒክ መሸነፋቸው ይታዎሳል።

የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሠልጣኝ ኤዲን ቴርዚች በበኩላቸው “እኛ ፍጹም የተለየ ቡድን አዋቅረናል። በመኾኑም ሪያል ማድሪድን አሸንፈን ዋንጫ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል” ብለዋል። በዶርትሙንድ በኩል ኮትዲቯራዊው አጥቂ ሰባስቲያን ሃለር ከባልንጀሮቹ ጋር ልምምድ ባለመሥራቱ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ኾኗል።

ሁለቱ ቡድኖች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች 14 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሪያል ማድሪድ ስድስት ጊዜ ሲረታ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ሦስት ጊዜ አሸንፏል። በአምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ዛሬስ ማን ያሸንፍ ይኾን? የስፔን እና የጀርመን ቡድኖች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለዋንጫ ለፍጻሜ ሲገናኙ ይህ ለአምስተኛ ጊዜ መኾኑ ነው።

የኾነ ኾኖ በዛሬው ጨዋታ ሻምፒዮና የሚኾነው ቡድን ከዋንጫ ሽልማት በተጨማሪ 21 ሚሊዮን ፓውንድ ተሸላሚ እንደሚኾን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል። ጨዋታውን ስሎቬኒያዊው ስላቮች ቪንሲች በዋና ዳኝነት ይመሩታል። የሀገራቸው ልጅ ኔጃክ ካጃታዞቪች የቫየር ዋና ዳኛ ኾነው ተመድበዋል።
የእግር ኳስ ጨዋታን ቅድመ ውጤት የሚገምተው ኦፕታ ኮምፒዩተር ሪያል ማድሪድ አሸንፎ ዋንጫ ይወስዳል ማለቱን ልብ ይሏል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here