የአፍሪካ ዋንጫ ባለውለታዋን ሀገር የሚወክለው ባምላክ ተሰማ።

0
358

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ዋንጫ ምስረታውን ሲያካሂድ ከእግር ኳስ ውድድር በላይ ዓላማ ነበረው። በአውሮፓዊያን ቅኝ ግዛት ጫንቃቸው ጎብጦ የነበረው አፍሪካዉያን ነጻነትን ለማግኘትና እርስ በእርስ ለመተባበር እግር ኳስ የመገናኛ ድልድይ ኾኖ አገልግሏል። ከቅኝ ግዛት ነጻ የነበረችው ኢትዮጵያ ቀሪ አፍሪካዊያን ነጻ እንዲወጡና የአፍሪካ ዋንጫ እንዲጀመር ትልቅ አስተዋጾኦ አድርጋለች።

በደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ሥርዓት የሰው ልጅ በቆዳ ቀለሙ ምክኒያት ብዙ ግፎች ሲፈጸሙም የአፍሪካ እግር ኳስ አባቱ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የእግር ኳስ ሥርዓቱ እንዲቃወም በማሰብ የማንዴላዋን ሀገር ከአፍሪካ ዋንጫ እንድትታገድ በማድረጋቸው አሁንም ድረስ በአፍሪካዉያን ዘንድ አንቱ የሚያስብል ከበሬታ አሰጥቷቸዋል።

የአፍሪካ ዋንጫ አሁን ትልቅ የውድድር መድረክ ነው። እንደ አፍሪካ ኒውስ ዘገባም የሳምታት እድሜ ብቻ የቀረው የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ለ 34ኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው። በኢትዮጵያ ፣ሱዳን እና ግብጽ የተመሰረተው ይሄ ውድድር አሁን 24 ሀገራትን ያፎካክራል።

የውድድሩ ባለውለታ ኢትዮጵያም ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ማንሳቷ ይታወሳል። ከዚህ ድል የዘለለ ግን ለውድድሩ እዚህ መድረስ የከፈለችውን ዋጋ የሚመጥን ታሪክ የላትም።

ይባስ ብሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ቅንጦት ከኾነበት ሰንብቷል። በኮትዲቫር በሚከናወነው የዘንድሮው ውድድርም ኢትዮጵያ አትሳተፍም።

በ34ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚወክላት ብሔራዊ ቡድን ማግኘት ያልቻለችው ሀገር በውድድሩ በዳኛ ባምላክ ተሰማ ስሟ ይጠራል። ባምላክ የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር የሚያዘጋጃቸውን የተለያዩ ውድድሮች በመዳኘት በብቃታቸው ብዙ ሙገሳን ማግኘት ችለዋል።

ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ጨዋታዎችን በሚገባ በመወጣት ከአፍሪካ አልፎ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የመዳኘት እድልም አግኝተዋል። በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የመሀል ዳኛ /ዋና ዳኛ/ኾነው ጨዋታዎችን እንዲመሩ 26 ዳኞች ተመርጠዋል።

ከእነዚህ ውስጥም ኢትዮጵያዊ ባምላክ ተሰማ አንዱ ናቸው። የባምላክ በዋና ዳኝነት መመረጥ ከእራሳቸው አልፎ በብሔራዊ ቡድናቸው ኮትዲቯር አለመገኘት ላዘኑ ኢትዮጵያውያን እንደመጽናኛ ይቆጠራል።

ዘጋቢ፡- በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here