ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጁድ ቤሊንግሃም የስፔን ላሊጋ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። በክረምቱ የዝውውር ወቅት ከጀርመኑ ቦርሲያ ዶርትመንድ ወደ ስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ ያቀናቀው እንግሊዛዊ ኮከብ በመጀመሪያው ዓመት የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ተመርጧል። በሲናግናል ኢዱና ፓርክ ከቦርሲያ ዶርትመንድ ጋር የጀርመን ቡንደስሊጋን ዋንጫ ለማንሳት ተቃርቦ በመጨረሻው ጨዋታ የተነጠቀው ኮከቡ በነጩ ቤት የሰመረ ጊዜ እያሳለፈ ነው።
በነጩ መለያ የደመቀው ቤሊንግሃም ከሪያል ማድሪድ ጋር ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል። በመጣበት የመጀመሪያ ዓመት የስፔን ላሊጋ ዋንጫን ከፍ አድርጓል። በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ደግሞ ለፍጻሜ ቀርቧል። ከቀድሞ ክለቡ ቦርሲያ ዶርትሞንድ ጋር በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ድል ከቀናው ሌላ ክብር ነው።
የ2023/24 የላሊጋው ምርጡ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ቢሊንግሃም 19 ግቦችን አስቆጥሯል። ስድስት ለግብ የሚኾኑ ኳሶችን ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል። ሙንዶ ዲፖርቲቮ በዘገባው ቤሊንግሃም ከሪያል ማድሪድ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ የውድድር ዘመን የ2023/24 የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን አሸንፏል ብሏል። ቤሊንግሃም በስፔን ሊሊጋ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች መካከል አንዱ መኾኑንም ዘገባው አመላክቷል። በውድድር ዓመቱ በሪያል ማድሪድ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው።
“ለዚህ ሽልማት በጣም አመሰግናለሁ፤ ሽልማቱን ማግኘቴ ትልቅ ክብር ነው” ማለቱን ሙንዶ ዲፖርቲቮ ዘግቧል። ጁድ ቤሊንግሃም የቡድን አጋሮቼ፣ አሠልጣኙ እና የክለቡ እስታፍ በእኔ ላይ ላሳዩት እምነት አመሰግናለሁ” ብሏል። በምርጥ ደጋፊዎች ፊት መጫወት ለእርሱ ክብር መኾኑንም ገልጿል።
ስካይ ስፖርት በላሊጋው አስደናቂ ብቃትን ያሳየው ጁድ ቤሊንግሃም የዓመቱ ምርጥ ተጨዋቾች ተብሎ መመረጡን ዘግቧል። ጁድ ቤሊንግሃም በላሊጋው ከባርሴሎና ጋር በተደረጉ የኤልክላሲኮ ጨዋታዎች አስደናቂ ብቃት ማሳየቱን እና ለድል ያበቁ ግቦችን ማስቆጠሩን ስካይ ስፖርት በዘገባው አስታውሷል።
እንግሊዛዊው ኮከብ ቤሊንግሃም የወቅቱ ምርጡ ተጫዋች እየተባለ እየተሞካሸ ነው። በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከፈረሙ ተጫዋቾች መካከልም ምርጡ ፈራሚ እየተባለ ሲሞካሽ መክረሙ ይታወሳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!