ኤሌክትሪክ ወደ ቀደመ ክብሩ ይመለስ ይኾን?

0
230

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንደኛ ዲቪዝዮን እየተባለ የሚጠራው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ውድድር በ1990 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሚል ስያሜ ከተተካ ወዲህ ሁለት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ኾኗል። ከዚያ በፊትም አንድ ዋንጫ አሸንፏል። በ1953 ዓ.ም የተመሠረተው እና መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የመብራት ሃይል የእግር ኳስ ክለብ ነባር ከሚባሉት ክለቦች አንዱ ነው።

በ1990 ዓ.ም የውድድር ዓመት የሊጉን ዋንጫ ወስዷል፤ በ1993 የውድድር ዓመትም ክብረወሰን በኾነ የዮርዳኖስ አባይ 24 ግቦች ታግዞ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በድጋሚ አንስቷል። በ1994 ደግሞ ዋንጫውን ይወስዳል ተብሎ ሲጠበቅ በቅዱስ ጊዮርጊስ ለትንሽ ተነጥቋል። በ1998 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ የአዲስ አበባ ዋንጫን አንስቷል።

በእንዲህ ዓይነት ስመ ጥርነት እና ተፎካካሪነት የሚታወቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ2010 የውድድር ዘመን ከፕሪሚየር ሊጉ ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርዶ ቆይቷል። ያሬድ ጌታቸው በክለቡ ፕሮጀክት አድጎ ከ1985 እስከ 1997 ዓ.ም ድረስም በአማካይ ተከላካይነት ተጫውቷል። ክለቡ ዋንጫዎችን ሲያሸንፍ ያሬድም አብሮ ነበር፤ በአምበልነትም ዋንጫ አንስቷል።

ያሬድ ክለቡ የራሱ ታዳጊ ቡድን (ፕሮጀክት) እና የእግር ኳስ ሜዳ መኖሩ ከጥንካሬዎቹ መካከል መኾናቸውን ገልጿል። ተጫዋቾችን ከፕሮጀክት ስለሚያሳድግ ተግባብቶ እና ተከባብሮ ለመጫዎት ምቹ እንደኾነም ተናግሯል። ታላላቆቹ ታናናሾቻቸውን እየመከሩ ያሳድጋሉ፤ ያበቃሉም ብሏል። ሁሉም ነገር የተሟላ ባይኾንም ለክለቡ ክብር ስንል በራሳችንም ጥረት የምናሟላቸው፤ ቢጎድሉም የምንችላቸው ችግሮች ነበሩን ይላል ያሬድ። በሱ ዘመን የአንድ ተጫዋች ደመወዝ 300 ብር እንደነበር አስታውሷል። ከምንም በላይ ግን የመብራት ኃይልን ማሊያ ለብሶ መጫዎት ትልቅ ክብር ነው ሲል ያስታውሳል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሁን ያለውን ጥንካሬ አስጠብቆ ለመቀጠል ማደግን ብቻ ሳይኾን በፕሪሚየር ሊጉ መቆየትን አስቦ ከወዲሁ መሥራት እንዳለበት ነው ያሬድ የመከረው። ነባር ተጫዋቾችን በማሳተፍ ጥንካሬን መጨመር እንደሚገባም ጠቁሟል። የክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አንዷለም ወርቁ ክለባቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሁለተኛው ጠንካራ እና ተፎካካሪ ክለብ ነው ይላል። ደጋፊ ማኅበሩ ከክለቡ ኃላፊዎች ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራም ተናግረዋል። በተደረገው የተቀናጀ ሥራ ጠንካራ ቡድን በመገንባቱም በከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ እንዳልተቆጠረበት ጠቅሰዋል።

የደጋፊዎች ማኅበር ከተመሠረተበት ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የደጋፊዎች ቁጥር ወጥ ባይኾንም እስከ አምስት ሺህ ደርሶ እንደነበር የገለጹት አቶ አንዷለም ቡድኑን ከሜዳ ውጪ እየሄዱ የሚያበረታቱ አባላት እንዳሉት ገልጸዋል። የደጋፊዎች፣ የክለቡ መሪዎች እና የአሠልጣኝ ጥምረት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ጠንካራ ቡድን እንዳደረገው ጠቅሰዋል።

እስከ 2014 የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ የቆየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ2015 የውድድር ዘመን ተመልሶ ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቅሏል። ይሁንና በዚያው ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ለመውረድ ተገድዷል። አቶ መንግሥቱ አባይነህ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የቦርድ አባል ናቸው። በ2015 ዓመት የውድድር ዘመን ኤሌክትሪክ ጥሩ አቋም ላይ አልነበረም ብለዋል። ነገር ግን በ2016 ዓ.ም የክለቡ ቦርድ ኅላፊዎች ሥራዎችን በመምራት ክለቡ የውድድር ዘመኑን በውጤታማነት እንዲያጠናቅቅ ማስቻሉን ነው ለአሚኮ የተናገሩት።

ከተጫዋች እስከ መሪ ጠንክሮ የሠራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ2016 የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው አምስት ጨዋታ እየቀረው ነው ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀሉን ያረጋገጠው። የክለቡ የቦርድ አባላት ከክለቡ የበላይ ጠባቂዎች ጋር በመመካከር የሦስት ዓመት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም አቶ አባይነው ጠቅሰዋል።

በዚህ መሰረት በ2018 የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት አቅዷል። ለዚህም በ2016 ምርጥ ቡድን፣ በ2017 ተፎካካሪ እና በ2018 ዋንጫ የሚያነሳ ቡድንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። የክለቡ ዋና አሠልጣኝ ሳምሶን አየለ በቡድናቸው በ2015 የውድድር ዘመን የተፈጠረው እንዳይደገም ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል። ከውስጥ አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች ማጠናከር እና ከውጪም በማዛወር ቡድኑን እያጠናከሩ መኾኑን ነው የገለጹት። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በእግር ኳስ ብቻ ሳይኾን በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት እና በቴኒስ ስፖርትም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here