ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አሠልጣኝ የማይበረክትለት ክለብ ነው ቼልሲ። ክለቡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሰባት ጊዜ የአሠልጣኝ ለውጥ አድርጓል። ክለቡ ሳይጠበቅ አርጀንቲናዊ አሠልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቸቲኒሆን ሸኝቶ አሁን ተረኛውን መፈለግ ጀምሯል።
በርካታ አሠልጣኞችም ስማቸው ከሰማያውዮቹ ጋር እየተነሳ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ክለቡን ከዚህ አሠልጥነው ያለፉት ቶማስ ቱሸል፣ አንቶኑዮ ኮንቴ እና ጆዤ ሞሪንሆ ይገኙበታል። ነገር ግን የቢቢሲ ስፓርት ዘገባ ቼልሲ አሁን ላይ ፍላጎቱን ወደ ወጣት አሠልጣኝ ፍለጋ አዙሯል።
የኢፕስዊች ታውኑ ኬረን ማኪና፣ የሌስተሩ ኢንዞ ማሪስካ እና የብሬንትፎርዱ ቶማስ ፍራንኪ ደግሞ የቼልሲ ምርጫዎች ናቸው ተብሏል። የሱቱትጋቱ አሠልጣኝ ሰባስቲያን ሁናስም ሌላኛው የቼልሲ እጩ ውስጥ የተካተቱ አሠልጣኝ ናቸው። ኬረን ማኪና ከቼልሲ በተጨማሪ በማንቸስተር ዩናይትድ የቴንሀግ ተተኪ እንዲኾኑ ፍላጎት አለ ሲል ቢቢሲ ሰፖርት አስነብቧል። አሠልጣኙ በዩናይትድ ቤት በምክትል አሠልጣኝነት ሠርተው ማለፋቸው ከቼልሲ ይልቅ ዩናይትድን ሊመርጡ ይችላሉም ተብሏል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!