ባየርን ሙኒክ ቪንሴንት ኮምፓኒን በአሠልጣኝነት ለማስፈረም ተቃርቧል፡፡

0
199

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አሠልጣኝ ኮምፓኒ ከእንግሊዙ በርንሌይ ቡድን ጋር ከ2023 ጀምሮ የሚታሰብ የአምስት ዓመት ውል አላቸው፡፡ ስለኾነም የበርንሌይ ቡድን ባለቤት አለን ፔስ ከባየርን ባለሥልጣናት ጋር በውል ማፍረሻ ክፍያ ዙሪያ ተነጋግረው ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎም ይጠበቃል። ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው የአንድ ሜትር ከ93 ሴንቲ ሜትር ለግላጋ የኾኑት የ38 ዓመቱ ቤልጄየማዊው አሠልጣኝ ኮምፓኒ እና የባየርን ሙኒክ ቡድን በብዙ ሐሳቦች ዙሪያ ተግባብተዋል፡፡ ቴሌግራፍ በበኩሉ ኮምፓኒ እና ባየርን ሙኒክ በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል፤ አሁን የኮምፓኒ ጥያቄ “ድጋፍ ሰጭ ባልደረቦቼን ወደ ሀገረ ጀርመን አሊያንዝ አሬና ስታዲየም እንድወስድ ይፈቀድልኝ” የሚለው ጉዳይ ብቻ ነው ሲል አስነብቧል፡፡ የኮምፓኒ ድርድር እውን ከኾነ በቡንደስሊጋው የውድድር ዘመን ያልተሳካላቸውን አሠልጣኝ ቶማስ ቱሄልን የሚተኩ ይኾናል፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው ባየርን ሙኒክ ቶማስ ቱሄልን እንደሚያጡ ካረጋገጡ በኋላ ተተኪያቸውን ለማግኘት ተቸግረዋል፡፡ ሙኒክ የባየሊቨርኩሰኑን አሠልጣኝ ዣቪ አሎንሶን፣ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ጁሊያን ኔግልስማን እና የአውስትራሊያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ራልፍ ራግኒክ ጋር ያደረጓቸው ግንኙነቶች አልሰመሩላቸውም፡፡ ቱሄል እንዲቆይ ስለማሳመን የተጀመረው ንግግር አዎንታዊ ድምዳሜ ላይ መድረስ ባለመቻሉ ባየርን ሙኒክ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል ነው የተባለው፡፡

ኮምፓኒ በሀገሩ ክለብ በአንደርሌክት እና በእንግሊዙ በርንሌይ ቆይታው ጥሩ ስም ገንብቷል፡፡ ምንም እንኳን በርንሌይን ከቻምዮንስ ሽፑ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አሳድጎ ባደገበት ዓመት ዳግም ቢመለስም አሠልጣኙ ተስፋ ሰጪ አቅም እንዳለው አሳይቷል፡፡ ከማንችስተር ሲቲ ጋር አራት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን ያሳካው ቤልጄማዊው ኮምፓኒ ከባየርን ሙኒክ ጋር እያደረገው ያለው ንግግር ከሰመረ በአሊያንዝ አሬና በታላቁ ቡድን በታላቅ ሥራ ይታያል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here