ለፓሪሱ ኦሎምፒክ ተገቢው ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የዝግጅት ኮሚቴው ገለጸ።

0
282

ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክን አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ የፓሪስ ኦሎምፒክ ዝግጅት ኮሚቴ ሁሉንም አካታች ባደረገ መልኩ ሥራወችን እየሠራ ስለመኾኑ ተገልጿል። በዚህም መሠረት አሁን ላይ አትሌቶች ሆቴል ገብተው ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ ነው፤ የኦሎምፒክ ችቦ በመላው ሀገሪቱ ክፍል እየተዟዟረ ይገኛል፤ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ተደርጓል፤ የክልል መንግሥታት ዝግጅቱን እንዲያግዙም ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ተብሏል።

በዚህ ውድድር ሚኒስተር መሥሪያ ቤቶችም ከአትሌቶች ጎን መኾናቸውን ለማሳየት ፓሪስ ላይ እንዲገኙም ዕድሉ ተመቻችቷል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ.ር) በፓሪስ ኦሎምፒክ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳተፈ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈም ዲያስፖራው በውድድሩ ተሳታፊ እንዲኾን ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

በፓሪስ ኦሎምፒክ ከ200 ሺህ በላይ ዲያስፖራዎች እንዲገኙ በፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርበት እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል ። አትሌቶችን ከሚያዚያ 28/2016 ዓ.ም ጀምሮ ሆቴል በማስገባት ዝግጅቶች እየተደረጉ መኾኑን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ናቸው። የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት ለዝግጅቱ ፈተና እንደኾነም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here