የሚቀናበት የባየር የሌቨርኩሰን የስኬት መንገድ!

0
274

ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጀርመን ሰማይ ሥር ብዙ አጃቢዎች የነበሩት አንድ ንጉሥ ነበር፡፡ ለዓመታት እርሱን የሚቀድም የጠፋ፣ ለዓመታት በክብር የተቀመጠ፣ ከዙፋን አልወርድም ያለ፡፡ እርሱ ሽምጥ ይጋልባል፤ ሌሎቹ የእርሱን አሯሯጥ እየተመለከቱ ከኋላ ይከተላሉ፡፡ እርሱ ክብሩን ይወስዳል፣ ሌሎቹ ከክብሩ ዝቅ ብለው ይቀመጣሉ፤ እርሱ ቀድሞ እንደሮጠ ቀድሞ ይጨርሳል፡፡

ዘንድሮ ግን ይህ አልኾነም በጀርመን አዲስ ንጉስ ተገኝቷልና፡፡ ለዓመታት የነገሠውን ንጉሥ ከዙፋኑ ጥሎ በዙፋን ላይ የሚቀመጥ፤ ለዓመታት የነገሠው ንጉሥ በታሪኩ አድርጎት የማያውቀውን ታሪክ የሠራ፤ በጀርመን ሰማይ ሥር አዲስ ታሪክ የጻፈ አዲስ ንጉስ፡፡ በጀርመን እግር ኳስ እንደ ባየርን ሙኒክ የነገሠ የለም፡፡ የቡንደስሊጋው ጨዋታ አሀዱ ብሎ ሲጀመር በዓመቱ መጨረሻ ላይ ባየርን ሙኒክ ዋንጫውን እንደሚያነሳው ይገመታል፡፡ ብዙ ጊዜም ግምቶቹ ሰምረው ሙኒክ ዋንጫውን ወደ አልያንዝ አሬና ይወስደዋል፡፡

በ2022/23 የውድድር ዘመን ተቀናቃኙ ቦርሲያ ዶርትመንድ የሙኒክን ክብር ሊነጥቅ ተቃርቦ በመጨረሻው ጨዋታ እጅ ሰጠ፡፡ ልማደኛው ሙኒክም ዋንጫውን የግሉ አደረገ፡፡ ቀድሞ ዋንጫውን የሚያነሳው ሙኒክ እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ መጠበቅ በዘመኑ ባላንጣዎች እንደተነሱበት ማሳያዎች ነበሩ፡፡

በ2023/24 የውድድር ዘመን ግን ጀርመናውያን፣ ባየርን ሙኒክ፣ አውሮፓ እና ዓለም ያልጠበቀው አዲስ ክስተት ታየ፡፡ ሙኒክ ባልጠበቀው ልዑል ተገርስሶ ዙፋኑን ተነጠቀ፡፡ የጀርመኑ ኀያል ክለብ ሙኒክ በቀድሞው ኮኮቡ ዣቪ አሎንሶ ክብሩን ተነጠቀ፡፡ ዣቪ አሎንሶ ባየርሊቨርኩሰንን ይዞ አዲስ ታሪክ ጻፈ፡፡

በስፔን የተወለደው ዣቪ አሎንሶ በዓለም ታላላቅ ሊጎች እና ታላላቅ ክለቦች ተጫውቷል፡፡ ከሀገሩ ጋርም በእግር ኳስ ዓለም ደምቋል፡፡ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር አንድ የዓለም ዋንጫ እና ሁለት የአውሮፓ ዋንጫዎችን ከፍ አድርጓል፡፡ በዘመኑ ምርጥ ከሚባሉ የመሐል ሜዳ ተጫዎች መካከል ነው ይባልለታል፡፡ በስፔን በኤባር፣ በሪያል ሶሲዳድ እና ሪያል ማድሪድ፣ በእንግሊዝ በሊቨርፑል፣ በጀርመን በባየርን ሙኒክ ተጫውቶ አልፏል፡፡

በዓለማችን ቁንጮ ከሚባሉ ተጫዎቾች ጋር ተጫውቷል፤ ለአብነት ከክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ከሰርጂዮ ራሞስ፣ ከፔፔ፣ ከኤከር ካሲያስ እና ከሌሎች ከዋክብት ጋር በማድሪድ፣ ከዣቪ ሄርናዴዝ፣ ከኢኒሽታ፣ ከቶሬስ እና ከሌሎች ከዋክብት ጋር በስፔን ብሔራዊ ቡድን፣ ከጄራርድ እና ከሌሎች ከዋክብት ጋር በሊቨርፑል፣ ከማኒዮል ኒዮር፣ ከፍራንክ ሪቨሪ፣ ከሮበን እና ከሌሎች ከዋክብት ጋር በባየርን ሙኒክ ተጫውቷል፡፡

ምን ይሄ ብቻ ዣቪ አሎንሶ በዓለማችን ምርጥ በሚባሉ አሠልጣኞችም ሠልጥኗል፡፡ ፔፕ ጋርዲዮላ፣ ጆሴ ሞሪኒሆ፣ ራፋ ቤኔቴዝ፣ ካርሎ አንቾሌቲን የመሳሰሉ ታላላቅ አሠልጣኞች በእግር ኳስ ሕይወቱ አሠልጥነውታል፡፡ ይሄም አሁን ለደረሰበት የአሠልጣኝነት ብስለት እና ለስኬቱ መሠረት ሳይኾንለት አልቀረም፡፡

ዣቪ ባየርሊቨርኩስንን ይዞ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ የቡንድስሊጋውን ዋንጫ የግሉ በማድረግ በቡንድስሊጋው የመጀመሪያው ክለብ እንዲኾን አድርጎታል፡፡ በክለቡ ታሪክም በሊግ ዋንጫ የተሞሸረ የመጀመሪያው አሠልጣኝ ኾኗል፡፡ የዣቪ አሎንሶው ቡድን የመጀመርያውን የሊግ ዋንጫ ክብር ቀድሞ ቢያረጋግጥም የመጨረሻውን ጨዋታ ኦግስበርግን ድል በማድረግ ያለሽንፈት ያጠናቀቀበትን ክብር አሳክቷል፡፡ ይሄም አዲስ ታሪክ ኾኗል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው፡፡

ሌቨርኩሰን ለ59 ዓመታት በአውሮፓ ክብረ ወሰን ኾኖ የኖረውን በርካታ ጨዋታዎችን ያለመሸነፍ ጉዞ የግሉ አድርጓል፡፡ በዓመቱ 51 ጨዋታዎችን ባለመሸነፍ የራሱን ክብረ ወሰን እያሻሻለ ነው፡፡ ላለፉት 59 ዓመታት ረጅሙ ያለመሸነፍ ክብረ ወሰን ኾኖ የኖረው የፖርቹጋሉ ቤኒፊካ ይዞት የነበረው ነው፡፡ ቤኔፊካ በ1963 እና በ1965 አርባ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ባለመሸነፍ ክብረ ወሰን ይዞ ኖሯል፡፡

ቀሪ ሁለት የፍጻሜ ጨዋታዎች ያሉት ሌቨርኩስን ሁለቱንም ጨዋታዎች የሚያሸነፍ ከኾነ በሁሉም ውድድሮች ሳይሸነፍ ሦስት ዋንጫዎችን በማንሳት ሌላ ታሪክ ይሠራል፡፡ ሌቨርኩሰን በኢሮፓ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ከጣሊያኑ አትላንታ ጋር ይጨዋታል፡፡ በጀርመን ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ ከካይዛስላውተን ጋር ይጫወታል፡፡

ሌቨርኩሰን በ34 የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች 28ቱን ድል አድርጓል፡፡ በቀሪዎቹ ደግሞ አቻ ወጥቷል፡፡ 89 ግቦችን በተቃራኒ ቡድን ሲያስቆጥር፣ 24 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል፡፡ ሌቨርኩሰን በሊግ ጨዋታ ለመጨረሻ ጊዜ የተሸነፈው ባለፈው ዓመት በቦሃም 3ለ0 በኾነ ውጤት ነበር፡፡ ሌቨርኩሰን ቀጣይ የሚጠብቁትን ሁለት የፍጻሜ ጨዋታዎች ድል የሚያደርግ ከኾነ 53 ጨዋታዎችን ባለመሸነፍ ክብረ ወሰኑን ከፍ ያደርጋል፡፡

ጥቅምት 2022 ሌቨርኩሰን የደረሰው ዣቪ አሎንሶ በቡድኑ ድንቅ ነገርን አድርጓል፡፡ ሚረር በዘገባው ዣቪ በመጣበት ዓመት ያሳየው ድንቅ ሥራ ሌቨርኩሰን በ2023/24 የውድድር ዘመን ብዙዎች ጥሩ የሚባል ጊዜ እንደሚያሳልፍ ቢገምቱም የውድድር ዘመኑን ሳይሸነፍ ያጠናቅቃል ብሎ የገመተ ግን አልነበረም ብሏል፡፡ ሌቨርኩሰን ግን ግምቶችን ሁሉ ሰባብሮ አዲስ ታሪክ ጻፈ፡፡ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ 90 ነጥቦችን የሠበሠበው ሌቨርኩሰን በቡንደስሊጋው በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ነጥቦችን በመሠብሠብ ሁለተኛው ትልቁ ውጤት ነው፡፡

ለሌቨርኩሰን በ120 ዓመታት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫ ነው ከፍ ያደረገው፡፡ ይህን ላደረገው አሠልጣኝም ጎዳና እስከመሰየም ደርሷል፡፡ ዣቪ አሎንሶ ስለ ውድድር ዘመናቸው ሲናገር ያሳለፍነው ወቅት በጀርመን ብቻ ሳይኾን ምን አልባት በአውሮፓም ልዩ ነው ብሏል። አርሰናል በ2003/04 ሳይሸነፍ የፕሪሚዬር ሊጉን እንዲሁም ጁቬንቱስ በ2011/12 የውድድር ዘመን የጣሊያን ሲሪኤን ሳይሸነፉ ዋንጫዋን ያነሱበትን ወቅት እናስታውሳለን፣ እኛም በአውሮፓ እግር ኳስ የዚህ ታሪክ ክፍል መኾን ይገባናል ማለቱን ሚረር ዘግቧል፡፡

ጎል ዶትኮም በዘገባው አዲስ ታሪክ የጻፈው ሌቨርኩሰን ገና ሩጫውን አላጠናቀቀም ይላል፡፡ አሁንም ሁለት ዋንጫዎች ፊት ለፊቱ አሉና፡፡ እነዚያን በድል መቋጨት አዲስ ታሪክ፣ አዲስ ክብር ነው፡፡ ሌቨርኩሰን እና አሎንሶ በጀርመን እግር ኳስ እስካሁን የሠሩት እጅን በአፍ የሚያስጭን ታሪክ ነው፡፡ ለወደፊትም እነሱ የሚደምቁበት ሌላውን ደግሞ የሚያስደምሙበት እድል በእጃቸው ይገኛል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here