የአሸናፊነት እና የእግር ኳስ ውበት ምሳሌ ጋርዲዮላ!

0
466

ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከስፔን ካታሎን ካምፕኑ፣ እስከ ጀርመን ሙኒክ አሊያንዝ አሬና፣ ከዚያም ተሻግረው እግሊዝ ማንችስተር ኢትሐድ በድል ላይ ድል የደረቡ ድንቅ የእግር ኳስ መሪ፡፡ በእግር ኳስ መጠበብ፣ ከተቀናቃኝ ልቆ መገኘት፣ ኳስን ተቆጣጥሮ ተቃራኒ ቡድንን ማስጨነቅ መገለጫቸው ነው፡፡

በስፔን ከሚገኙ ግዛቶች መካከል ካታሎን ውስጥ ነው ትውልዳቸው፡፡ የካታሎንን ነጻ ግዛትነት ይደግፋሉ ይባላሉ፤ መቀመጫውን ካታሎን ካደረገው ባርሴሎና ጋር የደም እና የአጥንት ያክል ግንኙነት አላቸው ይባልላቸዋል፡፡ በባርሴሎና ተጫውተዋል፡፡ በተጫወቱበት ክለብ አሠልጣኝ በመኾን ብዙ ክብሮችን አሳክተዋል፡፡ እኝህ ሰው የዘመናዊ እግር ኳስ ቀማሪ፣ በዘመኑ ካሉ አሠልጣኞች መካከል ግንባር ቀደሙ፣ ማራኪ እግር ኳስ የሚጫወት ቡድንን የሚሠሩ፣ ድል አድራጊ ብዙ ብዙ ተብሎላቸዋል ፔፕ ጋርዲዮላ።

አንዳንዶች ደግሞ ምንም እንኳ የእግር ኳስ ዕውቀታቸው የመጠቀ ቢኾንም በገንዘብ ላይ የተመሠረተ ቡድን በመገንባት ድል የሚያመጡ ናቸው እያሉ ይተቿቸዋል፡፡ ምን ይሔ ብቻ እርሳቸው ከባርሴሎና ከወጡ በኋላ አይሳካላቸውም ተብለው ነበር፡፡ ለአብነት ባርሳን ለቀው ሙኒክን ለመረከብ በወሰኑበት ጊዜ ፔፕ ያለ ሜሲ ምን ማድረግ ይችላሉ? ያለ ኢኔስታ፣ ዣቪ እና ቡስኬትስ?ምን ሊፈይዱ? ያሉ ብዙ ነበሩ።ከእትብታቸው መቀበሪያ ርቀው፣ በአዲስ ባሕል፣ በአዲስ ሀገር፣ በአዲስ ሊግ የጀርመኑን ኀያል ክለብ ባየርን ሙኒክን መረከብስ ይሳካላቸዋልን? ያላቸው በርካታ ነበር፡፡

እርሳቸው ግን በጀርመን ሄደው እምብዛም አልተቸገሩም፡፡ ነገር ግን ከሙኒክ ጋር የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ባለማንሳታቸው አላልናችሁም፣ እርሳቸው የሚችሉት በባርሳ ቤት ብለው ክፍተታቸውን የቆጠሩም አልጠፉም፡፡ እርሳቸው በጀርመን አዲስ አጨዋወት ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ተጫዋቾች የላቀ የብቃት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አደረጉ፡፡ ተጫዎቾቻቸው እና አድናቂዎቻቸው ጎራ ለይተው ሀሳብ አቀረቡ፡፡ አንድ እውነታ ግን አለ በዋንጫ የታጀበ ወርቃማ የአሠልጣኝነት ዘመን እንዳላቸው፡፡

በባርሴሎና እና በሙኒክ ወርቃማ ጊዜያትን አሳልፈው ማንቸስተር ሲቲ የደረሱት ፔፕ ጋርዲዮላ በእንግሊዝ ታሪኮችን መጻፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ እጅግ ብርቱ ፉክክር በሚደረግበት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ለአራተኛ ተከታታይ ዓመታት የሊግ ዋንጫን በማንሳት አዲስ ታሪክ ጽፈዋል፡፡ በፕሪሚዬር ሊጉ ታሪክ ያን ያክል የጎላ ስም ያልነበረውን ሲቲን የያዙት ፔፕ እርሳቸው ከያዙት በኋላ በፕሪሚዬር ሊጉ አይነኬው ቡድን አድርገውታል፡፡

የ2023/24 የእግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲጠናቀቅ አዲስ ታሪክ በመጻፍ ዋንጫውን ከፍ ያደረጉት ፔፕ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የስፖርት ቤተሰቦች አድናቆት እየተቸራቸው ነው፡፡ ቢቢሲ በዘገባው ፔፕ ጋርዲዮላ ማንቸሰተር ሲቲን በፕሪሚዬር ሊጉ የማይነካ ቡድን አድርገውታል ብሏል፡ በሀገር ውስጥ ዋንጫ የበላይነቱን የወሰደው ሲቲ አስደናቂ ታሪክ ጽፏል፡፡ ባለፉት ሰባት የውድድር ዘመናት ስድስተኛው ዋንጫ ወደ ሲቲ ካዝና ገብቷል ይላል ቢቢሲ በዘገባው፡፡ ይህን ያደረገው ሲቲ የማይነካ ቡድን መኾኑን አሳይቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፊታውራሪው ፔፕ ጋርዲዮላ ናቸው፡፡

በሊጉ በአስቶንቪላ ከተሸነፉ በኋላ ላለፉት 23 ጨዋታዎች ሳይሸነፉ ተጉዘዋል፡፡ 19 የሚኾኑትን ድል ሲያደርጉ በቀሪዎቹ ደግሞ አቻ ወጥተዋል፡፡ ፔፕ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ዋንጫውን የግላቸው በማድረግ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ የመጀመሪያው አሠልጣኝ ኾነዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ማንቸስተር ሲቲ በታሪኩ የቻምዮንስ ሊግ ዋንጫ እንዲያመጣ ያደረጉም አሠልጣኝ ኾነው ስማቸው በታሪክ ሰፍሯል፡፡

የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ ተከላካይ ኒዱም ኖንወሃ ሰዎች የትኛው ቡድን የተሻለ እንደኾነ እና በታሪክ ማን እንደሚመረጥ ክርክር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ነገርግን ማንቸስተር ሲቲ የትናንቱን ጨዋታ በማሸነፍ እና ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ ዋንጫ በማንሳት ያደረገውን ማድረግ የቻለ የለም ብሏል፡፡

የዌስትሐሙ አሠልጣኝ ዴቭድ ሞይስ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች በተደጋጋሚ የሊግ ዋንጫ አሸናፊዎች አይኾኑም የሚል ክርክር ነበር፡፡ ውኃ ሰማይዎቹ ግን ከፍ አሉ፡፡ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የሚገርም ድል ነው ማለታቸውን ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡ በእግር ኳስ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ለአሠልጣኙ አድናቆት አለው፡፡ ነገር ግን ከፔፕ ብዙ ነገር አለ፡፡ ጥሩ አሠልጣኝ፣ ተጨዋቾችን የመቆጣጠር ችሎታ ያለው ሲሉ አወድሰዋቸዋል ሞይስ፡፡

ፔፕ በ2016 ሲቲ ከደረሱ በኋላ 17 ዋንጫዎችን ማንሳት ችለዋል፡፡ እኒህ ድንቅ አሠልጣኝ እ.ኤ.አ. በ2019 ሲቲ በአንድ የውድድር ዘመን ሦስት የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን በማሸነፍ የመጀመሪያው ቡድን እንዲኾን አድርገውታል። ሲቲ ባለፈው ዓመት ደግሞ የአውሮፓ ቻምፒዮን ሊግ ዋንጫን ጨምሮ ሦስት ዋንጫዎችን በማሸነፍ ከምንጊዜም ባላንጣው ማንቸሰተር ዪናይትድ ጋር በታሪክ መስተካከል ችሏል፡፡

ፔፕ ታላላቅ ክለቦችን ብቻ አይደለም ታላላቅ ተጫዋቾችንም በማሠልጠን ይታወቃሉ፡፡ በባርሴሎና ሊዮኔል ሜሲ፣ ዣቪ ሄንዳንዝ፣ አንድሬስ ኢኔሽታ፣ ዝላታን ኢብራሄምሙቪች፣ ጀራርድ ፒኬ፣ ቡስኬት፣ ሳሙኤል ኢቶ፣ በባየርን ሙኒክ ማኑኤል ኒዮር፣ ማት ሐመልስ፣ ሮበርት ሊቫንዶስኪ፣አሪያን ሮበን፣ ፍራንክ ሪበሪን፣ ባስቲያን ሽዋንስታይገርን፣ በማንቸስተር ሲቲ ኩን አጉየሮ፣ ኬቬን ደብሮይን፣ ዳቪድ ሲልቫ፣ ቪንሰንት ኮምፓኒ፣ እና ሌሎች ታላላቅ ተጫዋቾችን አሠልጥነዋል፡፡

ፔፕ በ16 ዓመታት አሠልጣኝነት ሕይወታቸው 12 የሊግ ዋንጫዎችን ማሳካት ችለዋል፡፡ ጋርዲዮላ በአሠልጣኝነት በዘመናቸው ስድስት የፕሪሚዬር ሊግ እና ሦስት የቻምዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ 38 ዋንጫዎችን ማሳካታቸውን ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዬ ሮማኖ ጽፏል፡፡ አሁን ማንቸስተር ሲቲ በስፔናዊ አሠልጣኝ ስር ፕሪምየር ሊጉን ለተከታታይ አራት ዓመታት በማንሳት የመጀመሪያው የእንግሊዝ ክለብ ኾኗል። በታሪኩ የመጀመሪያ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን ያገኘው በእኝሁ ድንቅ አሠልጣኝ ነው።

በአንድ የውድድር ዓመት ሦስት ዋንጫዋችን በማሳካት በፈርጉሰኑ ዩናይትድ የተያዘውን ክብረወሰን የተጋርቱም በካታሎኑ ፍሬ የመሪነት ጥበብ ነው። ቀዩ የማንቸስተር ክፍል ደብዝዞ ሰማያውዩ እንዲጎላ ጋርዲዮላ በብዙ ይመሰገናሉ።ለዚህ ውለታቸው በኢትሃድ በስማቸው እየተዘመረላቸው ነው። ብዙዎች እንደሚስማሙበትም ጋርዲዮላ የሲቲ በመኾኑ ብዙዎች ይቀናሉ።ሲቲ ገንዘብ ሳይኾን ጋርዲዮላ እስካለው ድረስም በኅያልነቱ ይቀጥላል ባይ ናቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here