በሊጉ ማን ሻምፒዮን ይኾን?

0
335

ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የ2023/24 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት በሚደረጉ 10 ጨዋታዎች ይቋጫል። በተለይ ደግሞ ምሽት 12 ሰዓት ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ከዌስት ሃም ጋር የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ጨዋታ ያደርጋል። ሲቲ ይህንን ጨዋታ ዛሬ አሸንፎ ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ይኾናል የሚሉ በርካቶች ናቸው።

ዜጎቹ በታሪካቸው የሊጉን ዋንጫ ካነሱባቸው ሰባት ዓመታት አራቱን ያሳኩት በመጨረሻው ቀን ጨዋታ ነው። በ37 ጨዋታዎች በሰበሰባቸው 88 ነጥብ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ሲቲ ተጋጣሚውን ማሸነፍ ከቻለ በቀጥታ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ ሻምፒዮን መኾኑን ያረጋግጣል። የሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ስለ ጨዋታው በሰጡት አስተያየት ከሁለት ዓመት በፊት አስቶንቪላ እንዳደረገው ዌስት ሃምም እኛን ለማሸነፍ እንደሚጫወት እንገምታለን ማለታቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።

ጋርዲዮላ አክለውም “ጨዋታው ከባድ እንደሚኾን እጠብቃለሁ። ስለዚህ እኔም ኾንኩ ተጫዋቾቼ ከባዱን ፈተና በድል ለመወጣት ተዘጋጅተናል” ብለዋል። በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት አርሰናልም በሜዳው ኢምሬትስ እንደ ሲቲ ኹሉ ዋንጫውን ሊያነሳ የሚችልበትን ጨዋታ ከኤቨርተን ያደርጋል።
ቡድኑ ካደረጋቸው 37 ጨዋታዎች 86 ነጥብ በመሰብሰብ ከሲቲ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ዛሬ መድፈኞቹ ከ20 ዓመታት በኋላ የሊጉ ሻምፒዮን ለመኾን ከኤቨርተን ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ማሸነፍ ብቻ ሳይኾን የሲቲን መሸነፍ ወይም አቻ መውጣትንም ይጠብቃሉ። የአርሰናሉ አሠልጣኝ አርቴታ “መጀመሪያ አርሰናል ኤቨርተንን ማሸነፍ አለበት፤ ዌስት ሃም ሲቲን ከረታ ወይም አቻ ከተለያዩ ድሉን በደጋፊዎቻችን ፊት ማጣጣም እንችላለን” ብለዋል ሻምፒዮን የሚኾኑበት ዕድል ከ50 በመቶ በታች መኾኑን በመጠቆም።

ማንቸስተር ሲቲ የሊጉን ዋንጫ ካነሳ በ135 ዓመታት የእንግሊዝ ሊግ ታሪክ በአራት ተከታታይ የውድድር ዘመናት ሻምፒዮን በመኾን የመጀመሪያው ቡድን ያደርገዋል። የ38ኛ ሳምንት ሁሉም የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ምሽት 12 ሰዓት ይደረጋሉ። በዛሬው ጨዋታ የሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳል? አርሰናል ወይስ ሲቲ?

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here