የተረሳው ቪላ ከፍ ብሏል!

0
400

ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኡናይ ኢምሬው አስቶንቪላ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ መኾኑን አረጋግጧል፡፡ አስቶንቪላን ከመውረድ ጫፍ የተረከቡት ኡናይ ኢምሬ በ2022/23 የውድድር ዘመን ለኮንፈረንስ ሊግ ሲያበቁት፣ በ2023/24 የውድድር ዘመን ደግሞ በቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ እንዲኾን ማድረግ ችለዋል፡፡ ቪላ በኮንፈረንስ ሊግ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ድረስም ተጉዞ ነበር፡፡

ታላላቅ ክለቦች በሚገኙበት እና ከፍተኛ ፉክክር በሚታይበት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በአስደናቂ አቋም አራት ውስጥ ገብተው መጨረሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በሊጉ ከፍተኛ ስም ያላቸው ማንችስተር ዩናይትድ እና ቸልሲ ያላሳኩትን ክብርም አሳክተዋል፡፡ አስቶንቪላ የቻምፒዮን ሊግ ተሳታፊ መኾኑን ያረጋገጠው ቶተንሃም በማንችስተር ሲቲ መሸነፉን ተከትሎ ነው፡፡ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የተረታው ቶተንሀም ለቻምዮንስ ሊግ ተሳትፎ የነበረውን እድል አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ቶተንሀም ከማንችስተር ሲቲ ጋር የነበረውን ጨዋታ አሸንፎ ቢኾን ኖሮ የአራተኛነት ደረጃ እድሉን ያሰፋ ነበር፡፡ ነገር ግን በሲቲ መሸነፉን ተከትሎ እድሉን ለአስቶን ቪላ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ የመጨረሻ ጨዋታ የሚቀራቸው ሁለቱ ቡድኖች በመካከላቸው የአምስት ነጥብ ልዩነት አለ፡፡

የአውሮፓ ቻምፒዮን ሊግ ተብሎ ከተቀየረ በኋላ ቪላ በታሪኩ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ አያውቅም። በታሪካቸው ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወቱት ከ 41 ዓመታት በፊት የኢሮፓ ካፕ በሚባልበት ወቅት ነው፡፡ በወቅቱም የውድድሩ አሸናፊዎች ነበሩ። ኡናይ ኢምሬ የቻምዮንስ ሊግ ቦታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ይህ ልዩ ቀን ነው፤ ህልማችን ነው፣ የውድድር ዘመኑን የጀመርነው እዚህ ለመኾን ነው ብለዋል፡፡ ጉዳቶች አጋጥመዋቸው እንደነበር ያነሱት አሠልጣኙ በትኩረት በመጫወት ለቻምፒዮንስ ሊግ መብቃታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

አስቶን ቪላ ኡናይ ኢምሬን በ2022 ጥቅምት ወር ላይ ሲሾም ቡድኑ ከወራጅ ቀጣናው በሦስት ነጥብ ርቆ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ከእርሳቸው መምጣት በኋላ የክለቡ መንገድ የሰመረ ኾኗል። እርሳቸው ቪላን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ ከእርሳቸው ቡድን የተሻለ ነጥብ የሠበሠቡት ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና አርሰናል ብቻ ናቸው፡፡

በቢቢሲ መረጃ መሰረት ኢምሬ በታሪካቸው ስድተኛውን ቡድን ይዘው ለቻምዮንስ ሊግ ሲቀርቡ ነው፡፡ ከአሁን ቀደም ቫሌንሺያን፣ ስፓርታክ ሞስኮን፣ ሲቪያን፣ ፓሪስ ሴንት ዠርሜይን እና ቪላሪያልን ይዘው በታላቁ ውድድር ተሳትፈዋል። ከምንም በላይ ሰውየው የተረሳውን እና ላለመውረድ ይጫወት የነበረውን አስቶን ቪላ ለዚህ ማብቃታቸው ምስጋና እያስቸራቸው ነው።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here