ባሕርዳር፡ መስከረም 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ባለፉት ዓመታት በትምህርት፣ በጤና እና በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ መቆየቱን የደቡብ ወሎና አካባቢው አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበባው ታደሰ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
ለ2016 የትምህርት ዘመን 231 መማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ተጠናቀዋል ተብሏል፡፡ ለተጨማሪ መማሪያ ክፍሎቹ ግንባታ 176 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉንም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
በተለይም ደግሞ በዞኑ የሚታየውን የመማሪያ ክፍል እጥረት ለመቅረፍ ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው አቶ አበባው የገለጹት፡፡ ባለፈው ዓመት የተጀመሩ 231 የመማሪያ ክፍሎችን በማጠናቀቅ ለ2016 የትምህርት ዘመን ዝግጁ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ለግንባታውም 176 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉን ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪ የተገነቡት የመማሪያ ክፍሎች ከ9 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም አላቸው ተብሏል፡፡ በቀጣይም በዞኑ የሚታየውን የመማሪያ ክፍል እጥረት ለመፍታት በተለይም ደግሞ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አቶ አበባው አንስተዋል፡፡
አልማ በሚያስገነባቸው የትምህርት ተቋማት ላይ የማኅበረሰቡ ድጋፍ እና ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል ያሉት ኅላፊው ይኽም የግንባታ ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆኑ እረድቷል ብለዋል፡፡
አልማ በዞኑ ባለፈው ዓመት ካስጀመራቸው 141 የትምህርት፣ የጤና እና የሥራ እድል ፈጠራ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል 74ቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል ያሉት አቶ አበባው የቀሪዎቹ ግንባታ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት መዘግየቱን አንስተዋል፡፡ በቅርቡ አጠናቆ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!