“የደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲኾን ኢትዮጵያ ገንቢ ሚና ትጫወታለች” አቶ ደመቀ መኮንን

15

ባሕር ዳር: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተመድ የደቡብ ሱዳን ልዩ ተወካይና በተመድ የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ሀላፊ ኒኮላስ ሮላንድ ሌይቦርን ሃይሶም ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ውይይት አካሄደዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ፀጥታና ሰላም እንዲረጋገጥና የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲኾን ያላትን ሚና እየተወጣች መኾኑን ተናግረዋል።

በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን የታሪክ የባሕልና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኘነት መነሻ በማድረግ የቀጣናው ሰላም እንዲፀና እየሰራች መኾኑን ለልዩ ተወካዩ ኒኮላስ ሮላንድ ሌይቦርን ሃይሶም አስረድተዋል። በደቡብ ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ በሀገሪቱ አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ ኢትዮጵያ ለሰላም የሚደረገውን ጥረት ትደግፋለች ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በተቀናኞቹ መካከል መተማመን፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች ፣ተቋማት፣ ጉረቤት ሀገራትና ዓለምአቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባው አፅንኦት ሰጥተዋል።

በተመድ የደቡብ ሱዳን ልዩ ተወካይና በተመድ የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ኀላፊ ኒኮላስ ሮላንድ ሃይሶም ኢትዮጵያ የጉረቤት ሀገራት ሰላም እንዲረጋገጥ ያላት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተመድ ለሚያደርገው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ኢትዮጵያ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል።

በሚቀጥለው ዓመት በደቡብ ሱዳን የሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በአፍሪካ ኀብረት ፣ኢጋድ እና ተመድ በጋራ ለመሥራት የኢትዮጵያ ተሳተፎ ጉልህ በመኾኑ እገዛው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላም ማስከበር ተልኮ የምታደርገውን ድጋፍ ከተመድ ጋር በመኾን ያላትን አጋርነትና አስተዋጽኦ ልዩ ተወካይ አድናቆት ሰጥተዋል።

በጎረቤት ሀገራት በወቅታዊ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከሱዳን ፣ደቡብ ሱዳንና ከሌሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ወደ አገሪቱ እየገቡ ቢኾንም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተሟላ አገልግሎት በመስጠት እያስተናገደች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!