ባሕርዳር፡ መስከረም 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የጸጥታ ዘርፍ ቅኝት የሀገራትን ሉዓላዊነት ያከበረ፣ የባለብዙ ወገን ትብብር እና አካታችነትን የተከተለ እንዲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።
አቶ ደመቀ ይህን ያሉት «ሰላም፣ ብልፅግና፣ ለውጥና ዘላቂነት» በሚል መሪ ሃሳብ በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ኢትየጵያ ለመንግሥታቱ ድርጅት መመስረት ታሪካዊ ሚና እንደተጫወተች ሀገር የጋርዮሽ ዓለም እንዲኖር ትሻለች ብለዋል። የነበረው አካታች ያልሆነ መዋቅር የጋራ ፍላጎትን ለማስፈጸም የማያስችል በመሆኑ ሁላችንም በተባበረ መንገድ የባለብዙ ወገን ሥርዓት ለመዘርጋት አቋም ሊኖረን ይገባል ብለዋል።
ዓለምአቀፋዊ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን ከተፈለገ አዲሱ የዓለም የጸጥታ ሥርዓት የአባል ሀገራትን ሉዓላዊነት ያከበረ መሆን እንዳለበት ኢትዮጵያ በጽኑ እንደምታምን ነው አቋሟን የገለጹት። ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ድርጅት ሰላም ማስከር ተልዕኮ ስር ለዓለም ሰላም ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ ሀገር የጸጥታው ምክር ቤት ሪፎርም የምርጫ ሳይሆን ፍጹም አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ እንደምታምን ተናግረዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት አሳታፊ እና አካታች ሆኖ መዋቀር ያሻዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በምክር ቤቱ ለአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ የመስጠት ጉዳይ ፖለቲካዊ፣ ሞራላዊና ፍትሐዊ ውሳኔ የመስጠት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ለአፍሪካ የሰላም ተልዕኮ በቂ የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት እና ለሀገራት የሕግ ማስከበር ሥራዎች ስኬታማነት አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የተናጠላዊ ማዕቀብ እና ተገቢ ያልሆኑ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች የመንግሥታቱን ድርጅት መርህና አሠራር የሚጣረሱ በመሆኑ ኢትዮጵያ በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚጣሉ መሰል እርምጃዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊነሱ ይገባል ብላ እንደምታምን አንስተዋል።
በሉዓላዊ ሀገራት መካከል የሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በተናጠላዊ ማዕቀብ ሳይሆን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት መፍታት አማራጭ መሆን እንዳለበትም ነው ያነሱት። ኢትዮጵያና መሰል ታዳጊ ሀገራት የመንግሥታቱ ድርጅት አጠቃላይ ቅርጽ መስተካከል እንዳለበት ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
አሁንም ይበልጥ አካታች፣ ውጤታማና ለብዝሀነት የተመቸ እንዲሁም ታዳጊ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ አሠራር መዘርጋት እንዳለበት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የተቀላቀለችበት ‘ብሪክስ’ በዚህ ረገድ ትልቅ ምሳሌ መሆኑን አንስተዋል።
በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለልማት ግቦች ስኬት የፋይናንስ አቅርቦት ቢኖርም በታዳጊ ሀገራት ግን ፍትሐዊነት የጎደለው በመሆኑ ይህንን ለማስተካከል አዲስ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና ዓለም አቀፍ ትብብር ይፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊና የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመገንባት የልማት ግቦችን ቀርጻ እየሠራች መሆኗን ጠቅሰው፤ ለዚህ ግን አዲስ የሆነ አካታች ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላምና ዴሞክራሲ መስፈን ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ችግር የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ የመፍታት መርህ በፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መፍታት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።
ስምምነቱ በመልካም አፈጻጸም ላይ መሆኑን ጠቀሰው፣ ከሰላም ስምምነቱ ባሻገርም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ የሽግግር ፍትህ ለማስፈን እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ለኢትዮጵያዊውን የተሻለ እና ብሩህ ነገ ለመገንባት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!