ባሕር ዳር: መስከረም 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ በመባል ይጠራል፤ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው፡፡ ዓለም አቀፉን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ ላለፉት አምስት ዓመታት ገደማ እጅግ የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ እንቅስቃሴ እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ በየጊዜው የሚፈጠሩ ተደራራቢ ፈተናዎች ገጥመውት ተዳክሞ ቆይቷል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስከ ጦርነት ሰው ሰራሽ ችግሮች የፈተኑትን ዘርፍ ወደ ነበረበት ለመመለስ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ መስከረም 17 በየዓመቱ የሚከበረው የዓለም ቱሪዝም ቀን ደግሞ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚ ነው ተብሏል። የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሽ ግርማ መንግሥት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ ዘርፉን ለማነቃቃትም የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ በተለይ መስከረም የኢትዮጵያ መስህብነት ጎልቶ የሚወጣበት፣ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ ክብረ-በዓላት የሚበዙበት በመሆኑ የቱሪዝም ወር ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
መስከረም 17 ቀን የሚከበረው የዘንድሮው “የዓለም ቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ ደረጃ በደቡብ ምዕራብ ክልል ይከበራል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዘርፉን ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚ እንደሆነም አመልክተዋል። አዲስ ዓመትን ተከትሎ የሚመጡት በዓላት ለቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ያላቸው አበርክቶ ከፍ ያለ ነው ተብሏል፡፡ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከደቡብ ምዕራብ ክልል ጋር በመተባበር በዓሉን ሲያከብር በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ያሉትን የቱሪዝም ፀጋዎች በሰፊው ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ አቶ ስለሽ ጠቁመዋል፡፡ ክልሉ በርካታ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና የተፈጥሮ መስህብ ሃብቶች ያሉት በመሆኑ ጸጋዎቹን ለማስተዋወቅ አጋጣሚውን በአግባቡ መጠቀም ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡
በኮኖና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ተጎድቶ የነበረውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲነቃቃ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡ ጦርነቱ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በጥናት የመለየት እና መልሶ የማልማት ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል ሚኒስቴር ዴኤታው፡፡
“ቱሪዝም በአንድ ተቋም ብቻ የሚሰራ ዘርፍ አይደለም። የቱሪዝም ሥራ በመልካም ሥም ላይ የተመሰረተ ሰፊ ሥራ ነው። መልካም ሥም የሚመጣው ደግሞ በሚሰሩ የገጽታ ግንባታ ሥራዎችና በሚሰጡ መረጃዎች ላይ ይመሰረታል” ያሉት አቶ ስለሽ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አካባቢውን በማስተዋወቅ፣ መረጃ በመስጠት፣ ገጽታ በመገንባት፣ በኢትዮጵያዊ እንግዶችን በመቀበል እና በማስተናገድ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
አቶ ስለሽ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችም ለሀገሪቷ አምባሳደር ኾነው ዘረፉን እንዲደግፉ ጥሪ አስተላልፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!