“የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነትን ለማስቀረት ተቋማትና ኅብረተሰቡ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል” የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን

33

ባሕርዳር፡ መስከረም 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት ለማስቀረት ተቋማትና ህብረተሰቡ የድርሻቸውን እንዲወጡ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አሳሰበ።

በኢትዮጵያ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም በዓለምአቀፍ ደረጃ ከተቀመጠው የሃይል አጠቃቀም መስፈርት ያነሰና ብክነት የሚጎላበት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት ማለት በምንጠቀመው የኃይል መጠን እና ለማምረት በሚያስፈልው ኃይል መካከል ያለው ልዩነት ወይም ምርት ለማምረት ከሚያስችለው በላይ ኃይል መጠቀም መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዚሁ ዙሪያ ለኢዜአ ማብራሪያ የሰጡት የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ዳይሬክተር አቶ ዘውገ ወርቁ፤ በኢትዮጵያ ያለው የኃይል አጠቃቀም ከፍተኛ ብክነት የሚታይበት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከፍተኛ ሃይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች፣ የንግድ ቤቶችና ህንፃዎች የኃይል አጠቃቀም ብክነት የሚስተዋልባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኃይል መጠቀሚያ እቃዎች ከደረጃ በታች መሆን ሌላኛው ምክንያት ሲሆን ከኃይል ማሰራጫ እስከ ተጠቃሚዎች ለማድረስ ባለው ሂደትም ከፍተኛ የኃይል ብክነት አለ ብለዋል።

በመሆኑም የሃይል አጠቃቀም ብክነትን ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት በተለይም ተቋማትና ኅብረተሰቡ ድርሻቸውን እንዲወጡ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

ከሌሎች አገሮች አንፃር በኢትዮጵያ ብክነትን ለመከላከል ብሎም ለማስቀረት የተሰሩ ሥራዎች ዝቅተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ በብዙ መልኩ ሰፊ ሥራ ይጠይቀናል ብለዋል።

ከፍተኛ ኃይል በሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ላይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የሃይል አጠቃቀም ኦዲት እየተደረገ መሆኑን የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በፋብሪካዎች ዓለም አቀፍ የሃይል አጠቃቀም መስፈርት ተግባራዊ እንዲሆን ስልጠና የመስጠት እና የክትትል ስራ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ያለውን የሃይል ብክነት ለማስቀረትም ሀገር ውስጥ ለሚገቡ የኤክትሮኒክስ እቃዎች መስፈርት ተዘጋጅቶ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የአዳዲስ የህንፃ ግንባታዎች ንድፋቸው የኃይል ቁጠባን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን መመሪያ እየተዘጋጀ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!