መስከረም: 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ለ2016 አዲስ ዓመት ለመላ ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያውያንን አዲስ ዓመት በማስመልከት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት እና የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ.ር) የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በዓሉን በማስመልከት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መልዕክት አዲሱ ዓመት ለመላ ኢትዮጵያውያን የሰላምና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ.ር) እንዲሁ፥ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለአዲሱ ዓመት (እንቁጣጣሽ) እንኳን አደረሳችሁ ስል ልባዊ ደስታ ይሰማኛል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከተለመደው የጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር የተለየ የዘመን አቆጣጠር ያላት ሀገር መሆኗንም አስታውሰዋል።
በዚህም ተጨማሪ የጳጉሜን ቀናት አቆጣጠር ስርዓት እንዳላትና በዘንድሮው ዓመት አንድ ቀን ጨምራ ስድስት ቀን እንደነበረች ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
2016 ዓ.ም ተስፋ፣ ሰላምና ስምምነት የሚጠነክርበት፣ ለልማት የጋራ ራዕይ የሚሰነቅበት ሁኔታ ለመፍጠር በትጋት መስራት ይገባል ብለዋል ዶክተር ወርቅነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት የመልካም ምኞት መልዕክት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!