ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን በኢትዮጵያ ሲሚንቶ ዘርፍ፣ በማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲሁም በታዳሽ ኃይሎች ኢንቨስትመንት ላይ መሠማራት እንደሚፈልግ ገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው፤ በቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀመንበር በሚስተር ሊ ዚያንግ ከተመራው የልኡካን ቡድን ጋር በኢትዮጵያና በቻይና መካከል በቀጣይ ስለሚከናወነው የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ወ/ሮ ሰመሪታ፣ የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን በኢትዮጵያ በኃይል ማመንጫና በመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታዎች ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየ ግዙፍ የቻይና ካምፓኒ መኾኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ግዙፍ ካምፓኒና ከሌሎችም የቻይና ኢንቨስተሮች ጋር ተባብሮ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾኗን አስረድተዋል፡፡
የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀ መንበር ሊ ዚያንግ በበኩላቸው፣ ቡድኑ በኢትዮጵያ የተከዜ ኃይል ማመንጫን፣ የፊንጫ አመርቲ ነሽ ኃይል ማመንጫን፣ ገናሌ ዳዋ 3 ኀይል ማመንጫን እና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን አስታውሰዋል፡፡
ቡድኑ በቀጣይነትም በኢትዮጵያ በማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲኹም በታዳሽ ኃይሎች ኢንቨስትመንት የመሠማራት ፍላጎት እንዳለው መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ከቻይና ግዙፍ ካምፓኒዎች መካከል የሚጠቀስና በርካታ ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ያለው የኢንቨስትመንት ተቋም ነው። ከኃይል ማመንጫ ግንባታዎች በተጨማሪ በመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቤቶች ግንባታና በሌሎች በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሠማራ ተቋም ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!