የቻይና መንግስት በሰጠው የነፃ ትምህርት እድል አሸናፊ ለሆኑ ተማሪዎች ሽኝት ተደረገ።

127

ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቻይና መንግስት በሰጠው የነጻ የትምህርት እድል አሸናፊ ለሆኑ 26 ተማሪዎች አዲስ አበባ በሚገኘው የቻይና ኢምባሲ ሽኝት ተደርጓል።

በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የቻይና አምባስደር ዣዎ ዚዩአን ሀገራቸው በኢትዮጵያ የሚደረገውን የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን በዛላቂነት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

አምባሳደሩ አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ ትብብር የጋራ በሆኑ ጉዳዮች በዘላቂነት ለመሥራት እንደሚያስችል አብራርተዋል።

በትምህርት ሚንስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነትና ስኮላርሺፕ ዴስክ ኃላፊ ኢዶሳ ተርፋሳ (ዶ.ር) በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት በኢትዮጵያ የሰለጠነ የሰው ኃይል ግንባታ ሂደት ውስጥ የቻይና መንግስት እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ተማሪዎች ተጨባጭ እውቀት በመቅሰምና ወደ ሀገራቸው በመመለስ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ግምባታ የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በተደረገው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችና ቀደም ሲል በቻይና ትምህርታቸውን ተከታትለው የተመለሱ ምሁራን ልምዳቸውን አካፍለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!