የሽግግር ፍትሕ የግብዓት ማሰባሰብ ምዕራፍ እየተጠናቀቀ መኾኑን የፍትሕ ሚኒስቴር የባለሙያዎች ቡድን አስታወቀ።

43

አዲስ አበባ: ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባለሙያዎች ቡድኑ የሽግግር ፍትሕ አማራጭ ሃሳብ ላይ ሲደረግ የነበረውን ምክክር እና ግብዓት የማሰባሰብ ሂደት ተከትሎ የፖሊሲውን አስፈላጊነት፣ የውይይት መድረኮችን ሂደት፣ ግኝት እና የቀጣይ ሥራዎች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

14 አባላት ያሉት ቡድኑ በሰጠው መግለጫ እንዳመላከተው የሽግግር ፍትሕ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዋና ዓላማ በሕዝባዊ ምክክር የተገኙ ሃሳቦችን በማሰባሰብ ወደ ሕግ ማዕቀፍ ሰነድነት መቀየር ነው።

የሽግግር ፍትሕን አስፈላጊነት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የቡድኑ አባል ዶክተር ማርሸት ታደሰ እንዳሉት የሽግግር ፖሊሲ አማራጮች ላይ ሃሳብ ሲቀርብ ቆይቷል።

በመኾኑም በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ለተከሰቱ ሕፀፆች የሽግግር ፍትሕ ያስፈልጋል ብለዋል። ሀገራችን ካሳለፈቻቸው ችግሮች ተምረን ዓለም አቀፍ ልምዶችን አገናዝበን የሽግግር ፍትሕ ማምጣት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት፡-

👉ዘላቂ ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲኖር ማድረግ

👉በመደበኛ ሕግ መፍታት የማንችላቸውን የቆዩ ችግሮች ለመፍታት እና

👉ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ ነው ተብሏል።

ከዚህ ቀደም የተሞከሩ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች መኖራቸውንና ውጤታማ አለመኾናቸውን ያነሱት ዶክተር ማርሸት የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት አስፈላጊ ኾኗል ነው ያሉት። ለዚህም ማዕቀፉን የተሟላ እውነት እና የችግሮቹ መሠረታዊ ምክንያቶች ተለይተው እነዚህን ባገናዘበ መንገድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል ። በአሁኑ ወቅት የግብዓት ማሰባሰቡ ሂደት ተጠናቆ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ እየተሸጋገርን ነው ብሏል ቡድኑ።

አሁን ሀገራችን ካለችበት ወቅታዊ ኹኔታ አንፃር በሂደቱ ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ መኾናቸውን የጠቆሙት አባላቱ አሁን ትግበራ ላይ ሳንኾን ለትግበራው የሚያስፈልጉ የሕግ ማዕቀፎችን ለማዘጋጀት በሂደት ላይ መኾናችን መታወቅ አለበት ብለዋል።

በጥናት፣ በውይይት እና በተሳትፎ ሂደቱን ውጤታማ ማድረግ ይቻላል ነው የተባለው። በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሚያ የተከሰቱ ግጭቶች ለሂደቱ አስቸጋሪ መኾናቸውን የጠቆሙት አባላቱ ግጭቶች ቢኖሩም የሽግግር ፍትሕ ሂደት መጀመሩ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ለትግበራው ግን አንፃራዊ ሰላም መኖር ይኖርበታል ነው ያሉት።

ሌላኛው የቡድኑ አባል ዶክተር ታፈሰ ካሳ ያነሱት ጉዳይ በሂደቱ የሀገርና የሕዝብ ፍላጎትን እንዲሁም ባለቤትነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነበር ብለዋል። የሽግግር ፍትሕ የእስካሁኑ ሂደት 3 ደረጃዎች አሉት፡፡

👉ለውይይት የሚኾን የፖሊሲ አማራጭ ሃሳብ ሰነድ

👉ሃሳብ ማሰባሰብ፣ ውይይት ማካሄድና የተገኙ ግብዓቶችን ማደራጀት ወይም መፃፍ እና

👉ሀገራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ናቸው ።

ሂደቱ ከላይ ወደታች ብቻ ሳይኾን ከታች ወደላይ እንዲኾንም ተሰርቷል ተብሏል። በዚህም ሀገርና ሕዝብ የሚፈልገው፣ አሳታፊ የኾኑ ውይይቶች የሚመሩበት መርኽ ያለው እንዲኾን ተደርጓል ተብሏል፡፡

የውጭ ተፅዕኖ እንዳይኖር እና አስፈላጊ ሲኾን ብቻ ግንኙነት እንዲደረግ ተደርጓልም ነው ያለው ቡድኑ።

በእያንዳንዱ ውይይት 60 ሰዎች እንዲሳተፉ የተደረገ ሲኾን ከተሳታፊዎች 50 በመቶ የሴቶች ተሳትፎ እንዲኖር ተደርጓል ብለዋል። ውይይቶች ሲጀመሩ 59 ቦታዎች የተለዩ ሲኾን በ12 ክልሎች ፣ በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር ማከናወን ተችሏል። በአዲስ አበባ ከተለዩ 6 አካባቢዎች የተወሰኑ የሚቀሩ እንዳሉና ከመንግሥት ጋር የውይይት መድረክ ማካሄድ እንደሚቀር ተመላክቷል።

ዶክተር ካሳ በቀጣይ የሚሰሩትን ተግባራትም ጠቅሰዋል:-

👉የተሰበሰቡ መረጃዎችን እና የሃሳብ ግብዓቶችን ማደራጀትና መተንተን

👉 ረቂቅ ማዘጋጀት

👉ከዚህ ሂደት በኋላ ከመንግሥት ጋር የሚደረገውን ከፍተኛ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት እና የተዘጋጀውን ረቂቅ ለመንግሥት ማስረከብ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡

ሌላኛው በመግለጫው የተነሳው ጉዳይም የሽግግር ፍትሕ ከሀገራዊ ምክክር ጋር ተመጋግቦ የሚሄድ መኾኑም ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!