የመውሊድ በዓል ረቡዕ መስከረም 16/2016 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ተገለጸ።

131

ባሕርዳር፡ መስከረም 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ ) ረቡዕ መስከረም 16/2016 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ገለፁ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በዓሉን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድረዲን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የዘንድሮው መውሊድ የኢትዮጵያ አራተኛ ዙር የ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት በተካሄደበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ።

መውሊድን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት የተራቡትን በማብላት መሆን እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የታላቁ አንዋር መስጊድ ኢማም ሀጂ ጠሀ ሙሀመድ ሀሩን በበኩላቸው፤ መውሊድን ስናከብር አስተማሪያችን ፣አርዓያችን እና ፍቅርን ለዓለም ያስተማሩ የመጨረሻው ነብይ ነብዩ መሐመድ ሰ.ዐ.ወ ሥራቸውን ለኡማው ለማስተላለፍ ለማስታወስ ነው ብለዋል።

ፋና እንደዘገበው፤ በጋዜጣዊ መግለጫው በዓሉ የሰላምና የአንድነት እንዲሆንም መልክት ተላልፏል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!