ባሕር ዳር: መስከረም 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሕጻናት ትምህርት ቤት በሚሄዱበት የመጀመሪያው ቀን የመረበሽ፣ ያልተለመደ ሥሜት፣ ፍርሀት እና የወላጆቻቸው ናፍቆት ይፈትኗቸዋል፡፡ ይኽ አይነቱ ስሜት በሕጻናት ዘንድ የሚጠበቅ እንደኾነም የሥነ-ልቦና ባለሙያው አቶ ሙሉአዳም ታምሩ ይናገራሉ፡፡ ወላጆች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት የሚሔዱ ሕጻናትን በሥነ-ልቦና ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን የትምህርት ቤትን አካባቢ ማለማመድ እና በልጆች አእምሮ ውስጥ መጥፎ ነገር እንዳይፈጠር ቀድመው ማስረዳት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ሕጻናት ለአካባቢው እንግዳ መኾን፣ ማልቀስ፣ መረበሽ፣ ከወላጆቻቻችን አንለይም ማለት እና ሌሎችንም ችግሮች ሊገጥሟቸው ይችላሉ፡፡
ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዕውቀት የሚገበዩበት ምቹ ሥፍራ ነው፡፡ በዚህ ምቹ ሥፍራ የሚውሉ ተማሪዎች ሥነ-ልቦናቸው የተረጋጋ፣ አዳዲስ ዕውቀት የሚገበዩበት፣ ከአዲስ አካባቢ ጋር ተግባቢ እንዲኾኑ እና ወላጆች ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ባለሙያው አሳስበዋል፡፡ “የልጆችን የትምህርት ቤት ቆይታ ለማሳመር የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነው” ያሉት ባለሙያው መምህራን እና ወላጆች በተማሪዎቹ ጉዳይ የሚገናኙበት እና የሚመክሩበት ሥርዓትም ሊኖር ይገባል ነው ያሉት፡፡
ወላጆች ልጆቻቸው የትምህርት ቤታቸውን አካባቢ የሚወዱበት፣ ጓደኛ የሚያፈሩበት፣ ዕውቀት የሚገበዩበት መኾኑን ማስረዳት አለባቸው ብለዋል፡፡ የልጆቻቸውን ሥሜት መረዳት እና ወደ በጎ አቅም መቀየር እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡ የሥነ-ልቦና ባለሙያው ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ሲያሟሉ የልጆቻቸውን ሥነ-ልቦና እየገነቡ መኾኑንም ልብ ሊሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡
አንድ ተማሪ ተማሪ መኾኑ የሚታወቀው በለበሰው ዩኒፎርም (የተማሪዎች የደንብ ልብስ) በመኾኑ ልጆች ሳይሳቀቁ እንዲሄዱ ዩኒፎርማቸው ቀድሞ መዘጋጀት አለበት ብለዋል፡፡ የሥነ-ልቦና ባለሙያው ልጆች የትምህርት ቤቶቻቸውን መመሪያ፣ አሠራር እና መርህ እንዲረዱ ከመምህራን በተጨማሪ ወላጆችም ድርሻ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ወላጆች የልጆቻቸውን ሥነ-ልቦና በበጎ መንገድ መቅረጻቸው እና ቀድመው ማዘጋጀታቸው የመምህራንን ሥራ ከማቅለሉ በተጨማሪ ተማሪዎች ያልኾነ ሃሳብ ላይ እንዳይጠመዱ ይረዳል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!