የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች ተገቢውን ካሳ በወቅቱ እንዲያገኙ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ.ር) ገለጹ።

26

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ለልማት ተነሺዎች መከፈል የነበረበት ካሳ 21 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ቢኾንም እስካሁን ድረስ የተከፈለው 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብቻ መኾኑ በምክር ቤቱ ቀርቦ ነበር። 12 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገና ያልተከፈለ ካሳ መኖሩም ተገልጿል። የምክር ቤት አባላቱም የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች አስፈላጊውን የካሳ ክፍያ ማግኘት እንዳለባቸው በአንክሮ ገልጸው ቀሪው ካሳ በአስቸኳይ እንዲከፈላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

ለጥያቄው መልስ እና ማብራሪያ የሰጡት ርእሰ መሥተዳድሩ የልማት መሬቱ ከተለካ እና ግምቱ ከተሠራ በኋላ የሚመጣ ተጨማሪ የካሳ ጥያቄ ለመክፈል አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል። በልማት ምክንያት በትክክልም ቤታቸው የፈረሰባቸው እና ከይዞታ መሬታቸው የተነሱ አርሶ አደሮች ተገቢውን ካሳ በወቅቱ እንዲያገኙ ከፌደራል መንግሥት ጋር ንግግር እየተደረ ሥለመኾኑ ገልጸዋል።

“የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን የካሳ ግምት መክፈል የግድ ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ለዚህም በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!