“የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ጀግና ተማሪዎች የአማራ ሕዝብ የከፍታ ምልክቶች ናቸው” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር)

124
ባሕርዳር:የካቲት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የዕውቅና አሰጣጥ መርኃ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ተካሄዷል። በዚህ ዝግጅት ላይ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) “በውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ጀግና ተማሪዎቻችን የአማራ ሕዝብ የከፍታ ምልክቶች ናቸው” ” ሲሉ ተናግረዋል።
የክልሉ ጀግና ተማሪዎች ያስመዘገቡት የላቀ ውጤትም የተማሪዎች የታታሪነት ፣ የአስተዋይነት፣ የአርቆ አሳቢነት እንዲሁም የላቀ ጥበባቸው እና በራስ የመተማመናቸው ውጤት እንደኾነ ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። በከፍተኛ ውጣ ውረድ ውስጥ ኾነው ባስመዘገቡት የላቀ ውጤት የአማራ ሕዝብ የከፍታ ምልክት መኾን ለቻሉ ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ዶክተር ማተብ “የአማራ ሕዝብን ከፍታ የማስጠበቅ እና አሻሽሎ የማስቀጠል ጉዟችንን ከጀመርን ቆይተናል” ሲሉ ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ከፍታ፣ ክብር እና ጥቅም የተጠበቀባት ገናና ሀገር የመፍጠር ጉዟችን ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ሲሉም ተናግረዋል። የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ጀግና ተማሪዎችም የከፍታ ጉዞው ጅምር ውጤቶች ናቸው ብለዋል። ተማሪዎች በቀጣይ በሚኖራቸው የዩኒቨርሲቲ ቆይታ የአማራ ሕዝብ የከፍታ ምልክቶች መኾናቸውን ሳይዘነጉ፤ በላቀ ታታሪነት እና አስተዋይነት፣አርቆ አሳቢነት እንዲሁም በላቀ ጥበብ እና በራስ መተማመን ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ዶክተር ማተብ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቢሮ ኀላፊው በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን በጋራ በመፍታት የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ በርካታ ጀግና ተማሪዎችን ማፍራት እንደሚገባም ተናግረዋል። ዛሬ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የምንሠራው ሥራ የአማራን ሕዝብ ጥቅም ሊያረጋግጥ የሚችል እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት እና ዘላቂነት የተረጋገጠባት ገናና ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ትውልድ ለማፍራት ያለመ መኾን አለበትም ብለዋ። ይህን አይነቱን የትምህርት ሥርዓት ለመደገፍ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶክተር ማተብ የሕዝብን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ እና የከፍታ ታሪክን ለማስቀጠል ለትምህርት የቅድሚያ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!