“ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ ያስፈልገዋል” አቶ ደመቀ መኮንን

61

ባሕር ዳር: መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ እንዲደረግበት ጥሪ አቀረቡ።

78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በኒው ዮርክ ከተማ መካሄዱን ቀጥሏል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን የዘላቂ የልማት ግቦች የመሪዎች የፖለቲካ ፎረም ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ተካሄዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የዘላቂ ልማት ግቦች እና እ.አ.አ በ2015 በአዲስ አበባ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ስምምነት ላይ የተደረሰበት የአዲስ አበባ የተግባር አጀንዳ ሰነድ ትግበራ የአፈጻጸም ጉድለት እንዳለበት ገልጸዋል።

ለዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ የሀገር ውስጥ የሀብት ማሰባሰብ ጥረቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደረ አመልክተዋል።

በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት እየተደረገ ያለው የልማት ፋይናንስ በቂ ያልሆነ እና ፍትሐዊነት የጎደለው መሆኑንም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓቱ ማሻሻያ እና ለውጥ ያስፈልገዋል ያሉት አቶ ደመቀ፣ ሀገራት እና ተቋማት የእዳ ስረዛ ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱም አሳስበዋል።

አቶ ደመቀ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁን ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!